በትግራይ ክልል አስፈላጊ የህክምና መድሃኒቶች እና ቁሳቁሶችን የማቅረብ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

  • Time to read less than 1 minute
Tigray

የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለሶስተኛ ጊዜ ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲጀመር ያደረገ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን በመጀመሪያ ዙር ከዛሬ ሁለት ሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የክምችት መጋዘን ለሽሬ ቅርንጫፍ ግምታቸው ብር 6,433,408.47 የሚሆን ህይወት አድን መድኃኒቶችንና የህክምና ግብዓቶችን ማድረስ ችሏል፡፡ 


በሁለተኛ ዙርም ግምታቸው ብር 1,080,429.28  የሚሆን የጤና አገልግሎት ግብዓቶችን በመላክና ለሽሬ ሆስፒታልና ዘጠኝ ጤና ጣቢያዎች በማድረስ ለማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜም ግምታቸው ብር 1,713,410.35 የሚሆን ግብዓቶች  ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን ተጨማሪ የህክምና መድሃኒቶች እና ቁሳቁሶችን በመጓጓዝ ላይ ነው፡፡


በሌላ በኩልም በዚህ ሳምንት  አስፈላጊ የህክምና አቅርቦት ቁሳቁሶችን  የያዙ ሁለት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል 33.9 ሜትሪክ ቶን መሰረታዊ የህክምና እቃዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ መድሃኒቶች እና የቀዶ ጥገና መሳሪዎችን በመጫን መቀሌ ደርሰዋል፡፡ ሌሎች የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትም ተጨማሪ ጭነት ለመላክ ዝግጁ አድርገዋል፡፡


በግጭቶች የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት እና አገልግሎት ለማስጀመር  ከተለያዩ የስራ ክፍሎች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች እና ሰራተኞች ወደ ስፍራው በማቅናት መልሶ የማደራጀትና አገልግሎት የማስጀመር ተግባሩን በቅርበት የመደገፍ ስራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ። ይህ ተግባርም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡


ጤና ሚኒስቴር ፣ኢትዮጵያ
2015