የዘንድሮዉ የዓለም ጤና ጉባኤ “የዓለም ጤና ድርጅት 75 ዓመት ቆይታ፣ ህይወትን በማዳን፣ ጤና ለሁሉም ለማሳካት” (WHO at 75: Saving lives, driving health for all) በሚል መሪ ቃል በዛሬዉ ዕለት በስዊዘርላንድ ጀኔቫ መካሄድ ጀምሯል።
በጤና ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የተመራዉ ከፌዴራልና ከክልል ጤና ቢሮዎች የተዉጣጣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችንና የግሉ ጤና ሴክተር ተወካዮችን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጄኔቭ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ጽ/ቤት ጋር በጉባኤዉ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል ።
ዛሬ የተጀመረዉ 76ኛ የአለም ጤና ጉባኤ ለሚቀጥሉት ቀናት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚቀጥል ሲሆን የተለያዩ የጤና እና ጤና ነክ ጉዳዮች የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራትና ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት በጉባኤዉ እና በጎንዮሽ ስብሰባዎች የሚቀርቡበትና የተለያዩ የዉሳኔ ሰነዶች (resolutions) ቀርበዉ የሚፀድቁበትም ይሆናል።
ጉባኤዉ ከመጀመሩ በፊት በጄኔቫ ከተማ “ዎክ ዘቶክ!”የጎዳና ላይ ሩጫ የተካሄደ ሲሆን አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶችና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል።