የፈረንሳይ ኤምባሲ በአፋር ክልል የሚገኘውን የአብአላ ሆስፒታልን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ2.5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነደት ፈረመ 

  • Time to read less than 1 minute
memorandum

የፈረንሳይ አምባሳደር በኢትዮጵያ ረሚ ማርሻው ይህ አሁን የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ከዚህ በፊት ቃል በተገባው መሰረት የሚፈጸም እንደሆነ እና የመልሶ የማቋቋም ስራውም በ2 አመት ውስጥ የሚተገበር እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ ሆስፒታሉን መልሶ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችልም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ከአንድ አመት በፊት የደሴ ሆስፒታል መልሶ ማቋቋም ስራ መጀመሩን ያስታወሱት አምባሳደሩ የፈረንሳይ መንግስት በግጭት ለተጎዱ የጤና ተቋማት የሚዲርገውን ድጋፍ በመቀጠል በትግራይ ክልል የሚገኘውን የአድዋ ሆስፒታልን መልሶ ለማቋቋም የሚሆን የ1.5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ እና ይህም ድጋፍ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት ተጎደተው ለነበሩ በ3 ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ 3 ሆስፒታሎች የሚደረገው ድጋፍ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የፈረንሳይ አምባሳደሩ የመግባቢያ ሰነዱን በፈረሙበት ወቅት እንደተናገሩት ፈረንሳይ በኢትዮጵያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እንደምትደግፍ እና በጤና ሚኒስቴር እየተሰራ የሚገኘውን የጤና ተቋት መልሶ ማቋቋም የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል፡፡ 

ለአብአላ ሆስፒታል የተደረገው ድጋፍ በጦርነት ጉዳት ደርሶበት ለነበረው የአካባቢው ማህበረሰብ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ለማቅርብ እንደሚያስችል የተናገሩት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፤ የየፈረንሳይ መንግስት ለአብአላ ሆስፒታል መልሶ ማቋቋም ላደረገዉ ድጋፍ፣ ከዚህ ቀደም  ለደሴ ሆስፒታል ያደረገዉን ድጋፍ እና
የአድዋ ሆስፒታልን ለመደገፍ ቃል በመግባቱም ምስጋናቸውን አቅርዋል፡፡ ከአጋሮች ጋር በመሆን የሚሰራው የጤና ተቋትን መልሶ የማቋቋም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር ሊያ ተናግረው፤ በኤምባሲው በኩል የተደረገው ድጋፍ ወደ ፊትም በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማትም ድጋፍ መሰጠቱን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የፈረንሳይ አምባሳደር በግጭት ወቅት በአፋር ክልል ተገኝተው ክልሉን መጎብኘታቸውን እንዲሁም ቃል በገቡት መሰረት ስለተደረገው ድጋፍ በክልሉ ህዝብ ስም ምስጋና የቃረቡት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ፤ ከሌሎች የአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸው ተቋትን የማቋቋም ስራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ 

በነበረው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረው የአብአላ ሆስፒታል አገልግሎት የሚሰጠው ለአፋር ብቻ ሳይሆን አጎራባች ከሆኑት ከአማራ እና ትግራይ ክልል ለሚመጡ ተገልጋዮችም ጭምር በመሆኑ መልሶ የማቋቋም ስራው በርካታ ያካባቢውን ማህበረሰቦች ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት አቶ ያሲን፣ የተደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉ የደረሰበትን ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ይረዳል ብለዋል፡፡