ዲጂታላይዝድ የታካሚዎች የጤና መረጃ አያያዝ መተግበሪያ ‹‹ዌልነስ ፓስ›› የሙከራ ትግበራ ስምምነት ተፈረመ

  • Time to read less than 1 minute
Welfare Pass

የጤና ሚኒስቴር መተግበሪያውን  ወደ ስራ ለማስገባት ከማስተር ካርድ፣ ከጋቪ እና ከጄ ኤስ አይ ጋር ዛሬ ስምምነት ተፈራርሟል። 


የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ እቅድ ውስጥ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ  አሰጣጥ ስርዓት ለማጠናከር ጥራት ያለው መረጃ ማሰባሰብ፣ መተንተን እና መጠቀም ቁልፍ ተግባራት አድርጎ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው በዚሁ ወቅት ዲጅታል መተግበሪያው በሙከራ ደረጃ መጀመሩ በጤናው ዘርፍ ያለውን የመረጃ ስርዓት ለማዘመን እንደሚረዳ ገልፀዋል።


የታካሚዎችን የጤና መረጃ ስርዓት ፍሰትን ለማቀላጠፍ ማስተር ካርድ ‹‹ዌልነስ ፓስ›› የተባለው የዲጅታል መላ የሙከራ ትግበራውም በተመረጡ የጤና ተቋማት በ15 ወራት ውስጥ ለአንድ ሚሊዮን ተገልጋዮች ለማዳረስ የታለመ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 


ፕሮግራሙ የጤና መረጃ ስርዓቱን ለማሻሻልና የመረጃ አያያዙ ውሳኔ ለመስጠት በሚጠቅም መልኩ ለማድረግ እየተተገበረ ካለው የኤሌትሪክ መረጃ ስርዓት እና DHIS 2 ጋር በተናበበ መልኩ የሚሄድ ፕሮግራም መሆኑ የገለጹት ዶክተር ሊያ አውታረ መረብ በሌለበት ሁኔታ ሳይቀር የተገልጋዮችን የህክምና መረጃ ለማንበብ እንዲቻልና መረጃው ከተገልጋዩ ጋር የሚንቀሳቀስ ካርድ ዉስጥ የሚቀመጥ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 


በተጨማሪም የማስተር ካርድ ዌልነስ ፓስ በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን  አገራት የህጻናት የክትባት መርሃ ግብርን ዲጃታላይዝድ በማድረግ በሁሉም ጤና ተቋማት የተሻሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደረዳቸው ጠቅሰው የአገራችንን አገራዊ የጤና ምላሽ መርኃ ግብርን የዲጂታል የጤና መረጃን በቀላሉ በማግኘት የታካሚ እንክብካቤን ቀጣይነት እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል፡፡

 
ዶ/ር ሊያ ፕሮግራሙ እውን እንዲሆን በትብብር ለሰሩ  ለማስተር ካርድ፣ ለጋቪ እና ለጄኤስአይ እንዲሁም ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


የማስተር ካርድ ስትራቴጂክ ግረውዝ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ማይክል ፎርማን በመድረኩ ባስተለለፉት  መልእክት እንዳሉት ዌልነስ ፓስ ቴክኖሎጂውን በተለያዩ ምእራፎች ለመተግበር የታለመ ሲሆን የመጀመሪያ ምእራፉ በኮቪድ-19 የመከላካያ ክትባት ላይ ያተኮረ ሆኖ በመላ አገሪቱ የተመረጡ የጤና ተቋማት በገጠርና በከተማ እንደሚጀመር ገልጸው በሁለተኛው ምእራፍ በርከት ባሉ ተቋማት በህጻናት ክትባት፣ የእርግዝና እንክብካቤ እና ሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን አስረድተዋል።


ፕሮግራሙ ለአገሪቱ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት መሻሻል  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው ለተግባራዊነቱ ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ነው አምባሳደሩ ያስታወቁት፡፡


የጋቪ ሲንየር ካንትሪ ማናጀር ቲቶ ረዋሙሻጃ በበኩላቸው ጋቪ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በኮቪድ-19 መከላከል ብሎም በሌሎች ክትባትቶች ላይ ለረጅም ጊዜ እየሰራ እንደቆየ ጠቁመው አሁንም ይህን ፕሮግራም በመስራት ሂደት ውስጥ ተቋማቸው መሳተፍ በመቻሉ ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡


የጄ ኤስ አይ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ቢኒያም ጥላሁን ጄ ኤስ አይ በአገሪቱ የጤና ስርዓት ላይ ለረጅም ጊዜ ዘርፈ ብዙ ድጋፎች እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑንና የጤና መረጃ ልውውጥ ስርዓት ጥራት ላይ ሲሰራ እንደቆየ አስታውሰው በዚህ ፕሮግራም ትግበራ  ሂደትም ተቋሙ የተሰጠውን ሃላፊነት ለመወጣት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡