ኮቪድ-19 ጋዜጣዊ መግለጫ

የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ በዓለማችን  ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ሃገራት(ኢትዮጵያን ጨምሮ) ከጤናም ባለፈ  ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እያደረሰ ይገኛል፡፡ 

 

የጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካለትን በማሳተፍ በአገራችን ቫይረሱ ከመገኘቱ በፊትና ከተገኘም በኋላ የተለያዩ   የመከላከያና የመቆጣጠርያ  ዘዴዎችን በመንደፍና በመተግበር ዜጎችን  ከቫይረስ ለመከላከል እና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በመስራት ላይ ነን፡፡ 

በአገራችን የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ አቅማችንን በየጊዜው በማሳደግ እስከአሁን ለ1,683,558 ዜጎች የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን 114,834 (6.8%)  ሰዎች የኮሮና ቫይረስ  እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል፤  ከነዚህ ውስጥም የ1,769 (1.5%) በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ 


በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ለሕክምና ክትትል ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ 305 የሚሆኑት ጽኑ ህሙማን ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም ከ40 እስከ 45 የሚሆኑት ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ (Mechanical Ventilator) የሚጠቀሙ ናቸው፡፡  እስካሁን ባለው ሁኔታ የጽኑ ሕክምና ክፍል ከገቡት ውስጥ 59 በመቶ ያህሉ ሒወታቸው አልፍዋል፡፡


በአሁኑ ሰዓት የጽኑ ሕክምና አገልገሎት የሚፈልጉ የህሙማን ቁጥር በከፍተኛ  መጠን እየጨመረ በመሆኑ ( በተለይ በአዲስ አበባ) ከጤና ተቋማት የመቀበል አቅም በላይ እየሆነ መጥትዋል፡፡ 


ይህ ቁጥር በዚህ  ደረጃ ለማሻቀቡ በሕብረተሰባችን ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ ቸልተኝነትና መዘናጋት፤ በሽታው ጠፍቷል ወይም በሽታው በኔና በቤተሰቤ ብሎም በማሕበረሰቤ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብሎ ካለመረዳትና (low risk perception) እና እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትና ሚና አለመወጣቱ  እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 


አሁን ላይ በሕብረተሰባችን ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ቸልተኝነትና በዚህ ከቀጠለ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ እንደ ሀገር ካለን ውስን የጽኑ ህሙማን እንክብካቤ አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አለን፡፡ (ስላይድ ላይ ያለውን ዳታ)
የጽኑ ታማሚዎችና አጠቃላይ የበሽታው ሁኔታ በዚህ አሰሰቢ ሁኔታ ላይ ቢሆንም፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ ከዚያም አልፎ ጉዳዩን እንደ ቀልድ የመውሰድ አዝማሚያ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በኮቪድ እያጡ ያሉ በርካታ ወገኖችና ከከፍተኛ ስቃይ በኋላና በብዙ የባለሞያዎች ርብርብ ፈጣሪ ረድቷቸው የዳኑ ወገኖች ግን ጉዳዩ ቀልድ አለመሆኑን በትክክል ይመሰክራሉ፡፡


በመሆኑም ኮቪድ-19 እያደረሰብን እና ሊያስከትልብን የሚችለውን የሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የመከላከል ስራ ለአፍታም ቢሆን ጊዜ የማይሰጠው እና ለተወሰኑ ተቋማት የማይተው በመሆኑ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣  የሐይማኖት ተቋማት፣ የህብረተሰብ ክፍሎችና ፣ ልዩ ልዩ ማህበራት፣ ቤተሰቦች እና እያንዳንዱ ግለሰብ የመከላከያ መንገዶቸን የዕለት ተዕለት የህይወት ተግባራቸው አድርገው እንዲቀጥሉ አሳስባለሁ እማጸናለሁ፡፡ አዎ በርካታ የሁላችንም ርብርብ የሚፈልጉ ሀጋረዊ ጉዳዮች አሉን፡፡ የኮቪድ ወረርሽኝም አሁንም ከነዚህ አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል ነው፡፡ በተለይም ሁሉም አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና ግለሰቦች ሰራተኞቻቸውም ሆኑ ደንበኞቻቸው የቫይረሱ መከላከያ መንገዶችን መተግበራቸውን በመቆጣጠር ወረርሽኑን በመከላከል ስራ ላይ ያለመዘናጋትና ቸልተኝነት እንዲሰሩና በመመሪያ ቁጥር 30 የተቀመጡትን ግዴታዎች እኒዲተገብሩ አደራ እላለሁ!  


በአጠቃላይ ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር በመስጠት በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እጆቻንን በአግባቡ በማጽዳት፣ በተለይ ደግሞ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በአግባቡ በመጠቀም፣ አካላዊ እርቀታችንን በመጠበቅ እና የሰዎችን በአንድ ቦታ መሰባሰብን የሚያስከትሉ ሁነቶችን በመቀነስ   ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡


በመጨረሻም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችና እንዲሁም ባለድርሻ አካላት  ከዚህ ከፊታችን የተጋረጠብን የኮቪድ-19 ሀገራዊ ፈተና በሰው እና በማሕበራዊ ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እና የመልካም አስተዳደር ችግር ከማስከተሉ አስቀድመን ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ  በማድረግ በእያንዳንዷ ደቂቃ የምናከናውነው ቅድመ ጥንቃቄ በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እና አራዓያነት ሊሆን እንደሚገባ መልክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

  
አመሰግናለሁ
 
ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ!! 
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
ታሕሳስ 1 ቀን 2013
አዲስ አበባ 
 

 

 

Amharic