በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ እና አሁን እየተሰጠ ባለው የኮቪድ-19 ክትባት መርሃ ግብር ከጤና ሚኒስቴር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

Submitted by admin on Thu, 08/12/2021 - 16:23

እንደምናውቀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአለማችን ሆነ በሀገራችን ከፍተኛ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የዛሬው መግለጫ ትኩረት የሚያደርገው በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ነው፡፡ አሁን ሀገራችን ያለበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታ የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛው በኮቪድ-19 ክትባት ዙሪያ ይሆናል፡፡

 

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሀገራችን የወረረሽኙ ምጣኔ በአንፃራዊ ሁኔታ ከነበረበት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እነጂ ካለፉት 3 ሳምንታት ጀምሮ የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ በሆነ ፍጥነት እየጨመረ ይገኛል። በበሽታው የሚያዙ ፣ በጽኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ቀደም ካሉት ሳምንታት በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ለዚህ እንደማሳያ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡

 • ባለፉት 3 ሳምንታት ናሙና ከሰጡ ግለሰቦች የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸዉ አማካይ ሳምንታዊ ምጣኔ ከ2.8 ወደ 7.4 በመቶ ከፍ ብሏል(2.6 እጥፍ ጭማሪ)

 • ሳምንታዊ በሽታው የሚገኝባቸው አማካይ ቁጥር ከ831 ወደ 3,302 አድጓል (4 እጥፍ ጭማሪ)፡፡

 • ወደ ህክምና ማእከላት የሚገቡ ህሙማን ቁጥር የ2.5 እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት 324 ግለሰቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ይገኛሉ፡፡

 • ሳምንታዊ አማካይ የሞት ምጣኔ ከ13 ወደ 36 አድጓል(2.8 እጥፍ ጭማሪ)

 • በአንጻሩ ደግሞ የአፍና አፍንጫ መሽፈኛ ማስክ የሚጠቀመው ሰው ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል

  • /አ 59 በመቶ

  • ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ከተሞች 20 በመቶ

 • ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ወትሮ ሁኔታ ተመልሷል፡፡

 

በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዚህ ፍጥነት እጨመረ የሚሄድ ከሆነ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል። ይህ ደግሞ በኮቪድ-19 ህክምና ማዕከላት የሚሰጠውን አገልግሎት ላይ ጫና በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የአልጋ ፣ ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ እና ኦክስጂን እጥረት ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

ይህ የስርጭት መጠን ደግሞ አንድም በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት እየተከሰተ ያለው ሦስተኛ ዙር የኮቪድ-19 በሽታ የስርጭት ማእበል ችግር በኢትዮጵያ እየጀመረ እንደሆነ አመላካች ሲሆን ማህበረሰባችን በዕለታዊ እንቅስቃሴው ውስጥ የመከላከያ መንገዶችን መተግበሩ ላይ መቀዛቀዙንና እየተተዘናጋ መሆኑን እና አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች በማህበረተሰቡ እየተሰራጩ መሆኑን ያመላክታል፡፡

 

ስለሆነም በሌሎች ሃገራት በሶስተኛ ዙር (3rd wave) የኮቪድ 19 ማእበል ምክንያት የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት በአገራችን እንዳይከሰት እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ማስክ ማድረግ፣የእጅን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እና ርቀትን መጠበቅ ላይ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ማንኛውም ክፍተኛ ጥግግት የሚፈጥሩ ስብስቦችን እንዲቀንስ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በሙሉ አቅም ከመተግበር ጎን ለጎን ከመጋቢት 4, 2013 ጀምሮ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በተቀናጀ መልኩ በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በመስጠት እስካሁን ድረስ 2,254,270 (ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሀምሳ አራት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ) ለሚሆኑ ዜጎች የመጀመሪያ ዙር ክትባት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን የመጀመሪያዉን ዙር ወስደው 3 ወር ለሞላቸዉም የሁለተኛ ዙር ክትባት መስጠትም ተጀምሮ እስካሁንም ከ300 ሺህ ሰዎች በላይ ሰዎች ሁለተኛውን ዙር ክትባት ወስደዋል፡፡ በተጨማሪም አገራችን ኢትዮዽያ ከተለያዩ ሀገራትና አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅትና በትብብር በመስራት ክትባቶችን ወደ አገራችን የማስመጣት ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት የህረተሰብ ክፍሎች አስቀድሞ በተለዩት መሰረት ክትባቱን እንዲያገኙ በማስቻል እና በሂደትም ቀሪዉን የማህበረሰብ ክፍል ደረጃ በደረጃ በክትባቱ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

 

በዚህ መሰረት ባለፉት አራት ወራት በአለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 በሸታን በመከላከል ረገድ ውጤታማነታቸዉ የተረጋገጡ የአስትራዜኒካ እና የሳይኖፋርም የክትባት ዓይነቶችን ደህንናታቸዉን በማረጋገጥ ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገቡ በማድረግ ለሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሲሰጥ ቆይቷል። የምናስገባቸዉ ክትባቶች በአይነት የተለያዩ ሲሆኑ በሽታውን ከመከላከልና በበሽታው ሊደርስ የሚችለውን የከፋ ወረርሽኝና ሞት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳት ከመቀነስ አንጻር ተመሳሳይ ዉጤት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡

 

በቅርቡም የአሜሪካ መንግስት በኮቫክስ ፋሲሊቲ በኩል ክትባቶችን ለተለያዩ ሀገሮች ለግሷል፡፡ በዚህም መርሀግብር ለኢትዮጵያ የተለገሰው የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን 1.65 ሚሊየን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ተረክበናል፡፡ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት አንድ ዙር ብቻ የሚሰጥ የክትባት አይነት ሲሆን ልክ እነደማንኛዉም የኮቪድ-19 ክትባቶች ሁሉ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ደህንነቱ እና ውጤታማነቱ በአለምቀፍ የጤና ድርጅት/WHO/ እንዲሁም በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የቁጥጥርና ደህንነት ማረጋገጫ ሂደትን ያለፈ ነዉ፡፡

 

በአዲስ አበባ ካለዉ ከፍተኛ የኮቪድ ወረርሽኝ አንጻር ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የኮቪድ-19 ክትባት ላልወሰዱ እድሜያቸዉ ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ የሚሰጥ ሲሆን በተቀሩት ክልሎች እና ከተማ አስተዳድር እድሜያቸዉ ከ55 ዓመት በላይ ለሆኑ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸዉ ሁሉ በአዲስ አበባም ሆነ በሁሉም ክልሎች የክትባት አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ይሆናል፡፡ ለዚህም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራው ተጠናቋል፡

 

ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ በስራቸው ባህርይ ከብዙ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ የሥራ ግንኙነት ያለቸዉን ሰራተኞች በሁሉም ክልልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ይህም ከዚህ በታች የምዘረዝራቸውን ያካትታል፡፡

  • በትራንስፖርት ሴክተር በፌደራል እና በክልል የተሰማሩ ሁሉም የባስ፣ የታክሲ፣የባቡር እና የፐብሊክ ትራንስፖርት ሾፌሮች እና ረዳቶቻቸዉ

  • ሁሉም የግል እና የመንግስት ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ሰራተኞች

  • የፌዴራል እና የክልል የገቢዎች እና ጉምሩክ ሠራተኞች

  • የፌዴራል እና ክልል የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ሰራተኞች

  • የሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና የቱሪዝም ስራ ላይ የተሰማሩ

  • የፌዴራል እና ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት

  • የትምህርት ዘርፍ ላይ ያሉ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋም የሚሰሩ መምህራን እና ሰራተኞች - ከመዋለህጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት

  • የአረጋዊያንእና የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያ ማእከላት ላይ የሚሰሩ

  • በፌዴራል እና ክልል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የህግ ታራሚዎች እና የማረሚያ ቤቶች ሰራተኞች

  • የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች

  • ሁሉም በኤሌክትሪክ እና ዉሃ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች

  • ሁሉም የከተማ አስተዳድር ሰራተኞች

  • (የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች በመጀመሪያው ዙር ተካተው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በተለያየ ምክንያት ያልወሰዱ ካሉ መውሰድ ይችላሉ)

 

ከላይ በተጠቀሱት ውስጥ የሚካተቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸዉ የማህበረሰብ ክፍሎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የመንግሥት ጤና ተቋማት ክትባቱ የሚሰጥ መሆኑን አዉቀዉ መታወቂያቸውን እየያዙ በመሄድ እንዲከተቡ አሳስባለሁ። ከዚህም በተጨማሪ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ስደተኞች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች የጤና ቢሮዎች በሚያመቻቹት መንገድ የክትባት አገልግሎቱ ተጠቃሚ ይደረጋሉ፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በአዲስ አበባ ከነገ ዐርብ ነሀሴ 7.ጀምሮ የሚሰጥ ሲሆን.በሁሉም ክልሎች ደግሞ ከሚቀጥለው ሳምንት ዐርብ ነሀሴ 14 ጀምሮ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

 

በመጨረሻም እስካሁን በወሰድናቸው ሁሉን አቀፍና ዘርፈ ብዙ የተቀናጁ እርምጃዎች ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አኳያ ውጤቶችን አስመዝግበናል፡፡ ቢሆንም ሁሉን አቀፍ የኮቪድ መከላከል እና ምላሽ ስራዎች አሁንም ተጠናክረዉ መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም አሁንም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የማህረሰባችን ዋነኛ የጤና ስጋት በመሆኑ፡፡ ርቀትን መጠበቅ፣ የእጅ ንጽህናን መጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በአግባቡ መጠቀም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ደግሜ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም የኮቪድ ክትባት፤ የመያዝ ምጣኔንም ሆነ ከተያዙም ወደ ከፋ የመሄድ እድሉን እጅጉን የሚቀንስ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ክትባቱን በመከተብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የከፋ ችግር እንዳያስከትል በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ በመንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት፣ በሐይማኖት ተቋማት እና ሌሎች ትኩረት እንዲደረግ መልዕክቴን እና ጥሪዬን ከአደራ ጭምር ለማስተላለፍ እወዳለሁ!

 

አመሰግናለሁ!!