በጤናው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎችና አመራሮች እውቅና ተሰጣቸው

Submitted by admins on Wed, 11/04/2020 - 16:05

የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ ዓመታዊ የጤናው ዘርፍ ጉባኤዎች በሴክተሩ በህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት፣ በሙያ መስክ የላቀ ልዩ ስራና አገልግሎት እንዲሁም በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች የላቀ አገልግሎት ላለቸው ባለሙያዎችና አመራሮች እውቅና እየሰጠ መምጣቱ ይታወቃል፡፡


በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል በሚካሄደው የዘንድሮው 22ኛው ዓመታዊ የጤናው ዘርፍ ጉባኤ ላይም በጤናው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎችና አመራሮች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡


በዚህም መሰረት ዶ/ር መኮንን አይችሉህም፣ አቶ ደምሴ ደኔቦ እና ዶ/ር ከይረዲን ረዲ በህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት፣ አቶ በሃይሉ ታደሰ፣ ዶ/ር ከፍያለው ታዬ እና አቶ አለማየሁ ግርማ በሙያ መስክ የላቀ ስራና አገልግሎት እንዲሁም በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች የላቀ አመራርነት ደግሞ ወ/ሮ ኑሪያ የሱፍ፣ ዶ/ር ይገረሙ ከበደ እና ዶ/ር ሻሎ ዳባ የዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡


ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ከባለሙያነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አመራርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ዶ/ር ከበደ ወርቁንም ልዩ ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡


በተጨማሪም በኮቪድ 19 መከላከልና መቆጣጠር አስተዋጽኦ ላደረጉ ለሁሉም ክልልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማገልገል ላይ በሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች ስም የምስጋና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡፡