"ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጠንካራ ምላሽ፤ የማይበገር የጤና ስርዓትን መገንባት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡" የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ 

Submitted by admins on Wed, 11/04/2020 - 16:02

በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው 22ኛው ዓመታዊ የጤናው ዘርፍ ጉባኤና የአምስተኛው ዓመት የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግምገማን በይፋ የከፈቱት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት ባለፉት አምስት ዓመታት የመጀመሪያው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲተገበር መቆየቱን ጠቅሰው የዕቅዱ ትግበራ ውጤታማነትንም ለመገምገም በተካሄዱ ጥናቶችና ዳሰሳዎች የተቀመጡ ግቦችን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ባይቻልም ሃገሪቱ በዕቅድ ዘመኑ ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች በመቋቋም በጤናው ዘርፍ ወደታለመው የልማት ግብ ለመድረስ ውጤታማ ስራ መሰራቱንና በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


ዶ/ር ሊያ ለውጤቱ መገኘት ምክንያት የሆኑትንም ሲጠቅሱ እንደተናገሩት ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ የተቀረጹትን አራቱን የጤና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎችን ትኩረት ሰጥቶ መተግበር መቻሉ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም የወረዳ ትራንስፎርሜሽን፣ የመረጃ አብዮት፣ የጤና አገልግሎት ጥራትና ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማምጣትና ርህሩህ፣ ተገልጋይ አክባሪና ተንከባካቢ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራትን ለማሳካት በትኩረት መተግበሩም ለውጤቱ መገኘት ምክንያት መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡


ዶ/ር ሊያ ታደሰ አክለውም የ2012 በጀት ዓመት የ4ኛው ዓመት የወረዳ ትራንስፎርሜሽን የዳሰሳ ግምገማ ሪፖርትን ጠቅሰው እንዳቀረቡት 49 ወረዳዎች ሞዴል መሆን ሲችሉ 109 ወረዳዎች ደግሞ መካከለኛ አፈጻጸም አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይም በመጀመሪያ ደረጃ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከተዳሰሱ 1671 ተቋማት ውስጥ 298 ብቻ ሞዴል መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡


የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትን ለማሻሻል በተለይም ደግሞ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የተለያዩ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን የ2019 መለስተኛ የስነ-ህዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው ልዩነቶችን ማጥበብ የተቻለና በተለይም በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አራቱን የአርብቶ አደር ክልሎች እና ሰባት ዞኖች ያላቸውን የፕሮግራም አፈጻጸም ከሀገራዊ አፈጻጸም ጋር ለማቀራረብ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጠቁመዋል፡፡


የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እስካሁን የተመዘገቡትን ውጤቶች ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ጠንካራ የጤና ስርዓትን በመገንባት ማንኛውንም የጤና አደጋዎች መመከት ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ የነበረና በተለይም በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዚህ የሚያስፈልገው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑ የታየበት ነበር ብለዋል፡፡ በቀጣዩ የ2ኛው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ይህው ጉዳይ የሴክተሩ ቁልፍና ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ እንደሆነና የያዝነውን ዓመት የጤናው ሴክተር ዓመታዊ የግምገማ ጉባኤ የማይገበር የጤና ስርዓት መገንባት ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጠንካራ ምላሽ በሚል ዋና ጭብጥ ላይ ለማካሄድ የተወሰነውም በምክንያት እንደሆነ ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል፡፡


ባለፈው ዓመት የዕቅድ ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዘርፉ ለማስመዝገብ ከታለመለው ግብ ለመድረስ በአንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ትጽዕኖ ማሳደሩን ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡