"እኔ እጄን በአግባቡ እታጠባለሁ ሕይወትም አድናለሁ!" በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚቆይ እጅ የመታጠብ ንቅናቄ በይፋ ተጀመረ።

Submitted by admins on Fri, 10/16/2020 - 09:59

ለአንድ ወር የሚቆየው እጅ የመታጠብ ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ሰው እጁን በአግባቡ በመታጠብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ንቅናቄውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ እጅን መታጠብ የሚያስገኘውን የጤና ጠቀሜታ በመረዳት ከእጅ ንጽህና ጉድለት የተነሳ ከሚመጡ በሽታዎች እራሳችንን መከላከል ይጠበቅብናል ያሉ ሲሆን በይበልጥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እጅን በአግባቡ መታጠብ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ለመከላከል የሚኖረውን ጠቀሜታ በመረዳት የአለም ጤና ድርጅት በሚመክረው መንገድ ለሃያ ሰከንድ እጅን በሳሙና በአግባቡ መታጠብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ዶክተር ሊያ ታደሰ አክለውም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሌሎች እጅን በአግባቡ ባለመታጠብ ምክንያት ከሚመጡ በሽታዎች በተጨማሪ የአይን ኢንፌክሽን፣ ከንጽህና ችግር የሚከሰቱ በሽታዎች እንዲሁም በጤና ተቋማት የሚከሰቱ የኢንፌክሽን ህመሞች ለመቅረፍ የእጅ ንጽህናን ለመጠበቅ ተገቢው የአቅርቦት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን በቅርቡ ትምህርት ሊከፈት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በትምህርት ቤቶች ያለውን የመታጠቢያ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተገቢው ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማትዮስ በትምህር ቤቶች ውስጥ እጅን መታጠብ ባህል እንዲሆን በስርአተ ትምህርቱ ተካቶ እንደሚሰራ የተናገሩ ሲሆን የዩኒሴፍ የዋሽ ሃላፊ ሚስተር ኪትካ ጎዮል በበኩላቸው እጅን በመታጠብ እራሳችንን ተላላፊ በሽታዎች መጠበቅ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ንቅናቄ የታለመለትን አላማ ለማሳካት በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ እና በሀገራችን ለ12ኛ ግዜ በሚከበረው የእጅ የመታጠብ ቀን ይፋ የተደረገው ንቅናቄ ለአንድ ወር ይቆያል፡፡