የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በማህበረሰቡ ዘንድ የሚደረገው ጥንቃቄ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል- የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

Submitted by admins on Wed, 07/08/2020 - 10:58

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደስ አለማቀፍዊ እና ሀገራዊ ስጋት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በዓለም አቀፍ፣ በአፍሪካ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙ በስፋት እየተሰራጨ፤ አሁን ያለበትም ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው የሚደረገው ጥንቃቄ ከወትሮው ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናገረዋል፡፡


በአጠቃላይ እስካሁን የላብራቶሪ ምርመራ ከተደገላቸው 266,323 ሰዎች ውስጥ 6,666 ሰዎች ቫይረሱ የተገኝባቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል 3,199 ሰዎች ማለትም 47 በመቶ ማገገማቸውን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡ 


የኮቪድ 19 ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ከውጭ ሃገር በአየር መንገድ በኩል የሚገቡ ተጓዦችን አስመልክቶ በአፈጻጸም ረገድ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት በቦሌ አየር መንገድ በኩል የሚገቡ መንገደኞች ከኮቪድ -19 ነጻ ስለመሆናቸው የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ይዘው ከመጡና በአየር መንገዱ በሚደረግ ተጨማሪ የሙቀት ልኬት መሰረት ለ14 ቀን በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ በማሻሻያው መካተቱን አስታውሰው በዚህ ማሻሻያም ከውጭ አገር የሚመጡ ተጓዦች የአንቲ ቦዲ ምርመራ ሳይሆን የአንቲጅን የምርመራ ምስክር ወረቀት ይዘው ሊመጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


ሰሞኑን ከተወዳጁ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ችግር ምክንያት አጠቃላይ የመመርመር አቅም ቀንሶ እንደነበር ተናግረው በህብረተሰቡ ዘንድ ከታየው የጥንቃቄ ጉድለት ጋር ተያይዞ ስርጭቱ ይጨምራል የሚል ስጋት ፈጥሯል ብለዋል፡፡


በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ /ጭምብል/ ማድረግ እጅን በሳሙና እና በውሃ በአግባቡ መታጠብ እንዲሁም አካላዊ እርቀትን በመጠበቅ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሚኒስትሯ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡