በሀገር አቀፍ ደረጃ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ 

Submitted by admins on Wed, 07/08/2020 - 10:31

ኢትዮጵያ የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል ብሎም የህብረተሰብ የጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ በመደበኛ ክትባት በ9 ወር ዕድሜያቸው ከሚሰጣቸው የመጀመሪያ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በተጨማሪ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ህጻናት እድሜያቸው 1 ዓመት ከ3 ወር ሲሞላቸው የ2ኛውን ዶዝ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ በመደበኛ የክትባት መርሃ-ግብር ተካቶ በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል ፡፡ 


ዶ/ር ሊያ አክለውም በሀገራችን በሁለት እና ሶስት ዓመታት ልዩነት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻዎች በተለያየ ግዜ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው በዘንድሮውም አመት ከሰኔ 23/2012 ዓ/ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ክትባቱ በዘመቻ መልክ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው በዘመቻውም እድሜያቸው ከ9 ወር እስከ 5 አመት ያሉ ህፃናት ከአሁን በፊት ክትባቱን ቢከተቡም ባይከተቡም ክትባቱ እየተሰጣቸው  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 


የክትባት ዘመቻው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት መስጠት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያትን ዶ/ር ሊያ ሲያስረዱ እንደተናገሩት የኩፍኝ በሽታ ህጻናትን ለህመም፣ ለአካል ጉዳት እና ሞት የሚዳርግ ስለሆነ እንዲሁም በአሁን ሰዓት በሁለውም የሀገራችን አካባቢዎች የኩፍኝ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ በመሆኑ በኩፍኝ ወረርሽ ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ህጻናት ቁጥር ብዙ ሊሆን ስለሚችል በዚህ ባለንበት እጅግ በጣም ፈታኝ ወቅት ዘመቻውን ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል፡፡


የክትባት ዘመቻ በስኬት ለማጠናቀቅ የሀይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የአካባቢ ሽማግሌዎች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሕብረተሰቡ ለክትባቱ ዘመቻ የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዶ/ር ሊያ ያሳሰቡ ሲሆን በዚህ ዘመቻ የክትባት አገልግሎቱን የሚሰጡ ጤና ባለሙያዎች እና ህጻናትን ይዘው ወደ ክትባት መስጫ ጣቢያዎች የሚመጡ ወላጆች የኮሮና በሽታን ለመከላከል የሚያስችል የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ፣ እጅን በሳሙና እና በንፁህ በውሃ በመታጠብ ወይም ሳኒታይዘር በመጠቀም እንዲሁም አካላዊ እርቀትን በመጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቅ ሊደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡      


የእናቶች እና ሕጻናት ጤና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው እንደተናገሩት የክትባት ዘመቻው ከተጀመረበት ከሰኔ 23/2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ 5,209,321 ዕድሜያቸው ከ9-59 ወራት የሆኑ ህጻናት ይህም ማለት ከታቀደው 35 በመቶ በዘመቻው መከተባቸውን አስረድተዋል፡፡ 


እድሜአቸው ከ 9 ወር እስከ 5 ዓመት ድረስ ያሉ 15 ሚሊዮን ህጻናት የኩፍኝ ክትባት ዘመቻው ተጠቃሚ ተደራሽ እንደሚሆኑ በመግለጫው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

Dr. Tegene Regassa    Media