መደበኛ የጤና አገልግሎቶች በነበሩበት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለፀ

Submitted by admins on Fri, 04/24/2020 - 12:01

የኮቪድ-19ን ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ አንድ አንድ የጤና ተቋማት አገልግሎት ማቆማቸው በመደበኛው የጤና አገልግሎቶች ላይ መስተጓጎል እንዳስከተለ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ለኮሮና ቫይረስ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከተለዩት የጤና ተቋማት ዉጪ ሁሉም የጤና ተቋማት እንደተለመደው መደበኛዉን የጤና አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ደረጀ አያይዘውም በተለይ በእናቶች እና ህፃናት ጤና አገልግሎት፣ ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ህክምና ላይ መደበኛ አገልግሎት መስጠታቸውን የሚከታተል ግብረ ሀይል ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት የህክምና ተቋሞቻቸውን የዘጉ የግል ጤና ተቋማት እንዳሉም የተደረሰበት ሲሆን ተግባራቸው ትክክል እንዳልሆነ እና በፍጥነት ሁሉም ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ይደረጋል።

ሕብረተሰቡም ወረርሽኙን ለመከላክል የሚደረገዉን ጥረት በማገዝ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት በሚሄድበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫውን ሊንኩን ተጭነው ማግኘት ይችላሉ:

http://www.moh.gov.et/ejcc/am/Press_Release

አለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ወሳኝ የሆኑ የጤና አገልግሎቶችን ለማስቀጠል የወጣ ማስፈፀሚያ:

http://www.moh.gov.et/ejcc/am/COVID19