የመቀንጨር ችግርን ለመቅረፍ የተያዘውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ ጥሪ ቀረበ

Submitted by dawit.berhanu on Fri, 11/22/2019 - 09:53


የብሔራዊ ስርዓተ ምግብ ፕሮግራም ዓመታዊ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡


ከስርዓተ ምግብ መስተጓጎል ጋር ተያይዞ የሚመጡት እንደ መቀንጨር ያሉ ችግሮች ከቅርብ አመታት በፊት ትኩረት ሳያገኙ በመቆየታቸው አሁን ላይ ርብርብ የሚጠይቁ ጉዳዮች መሆናቸውን በመድረኩ ላይ የተገኙት የባለድርሻ አካላት መስሪያ ቤቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ገልፀዋል፡፡


የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ከአሁን በፊት በተከተልነው አካሄድ አሁን ላይ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ ለወደፊት ደግሞ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ያስቀመጥነው ግብ ጋር ለመድረስ የሚያስችል ስትራቴጂና ስልት መከተል ያስፈላጋል ብለው ለዚህ ደግሞ እንደ ግብአት የሚጠቅሙ ከጉባኤው እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡


መንግስት የስርዓተ ምግብ ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ባለፉት ዓመታት በትኩረት እየሰራበት ይገኛል ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ሲሆኑ የሰቆጣ ስምምነት እና የምግብና ስርዓተ ምግብ ፖሊሲ መዘጋጀቱ ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡


የ2011 ዓ.ም. እቅድ አፈፃፀም ግምገማ፣ መልካም ተሞክሮዎች ላይ ልምድ መለዋወጥ እና የ2012 ዓ.ም. የትኩረት አቅጣጫዎች በመድረኩ የሚዳሰሱ ዋና ዋና ይዘቶች መሆናቸውን በጤና ሚኒስቴር እናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም ገልፀዋል፡፡ የስርዓተ ምግብ ጉዳይ የአካል ብቻ ሳሆን የአእምሮም ነው ያሉት ዶ/ር መሰረት ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር ስርዓተ ምግብ ላይ መስራት አለብን ብለዋል፡፡ የመቀንጨር ችግርን በ2030 ለመቅረፍ የተያዘውን እቅድ ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ዶ/ር መሰረት ዘላለም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡


የቀረበው ፅሑፍ እንደሚያሳየው የመቀንጨር ችግር እ.ኤአ በ2000 በአገር ደረጃ በአማካይ ከነበረበት 58 በመቶ በ2019 ወደ 37 በመቶ የቀነሰ ሲሆን የሰሜኑ የአገራችን ክፍል በ40 በመቶ ከፍተኛውን ቦታ ሲይዝ በአንፃራዊነት ጋምቤላ እና አዲስ አበባ የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡


“የተጠናከረ ዘርፈ ብዙ የስርዓተ ምግብ ቅንጅት የምግብ አለመመጣጠን ችግርን ለመግታት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው መድረክ እስከ ህዳር 13/2012 ዓ.ም እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡