አዲሱ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ፓኬጅ ይፋ ተደረገ

Submitted by dawit.berhanu on Wed, 11/13/2019 - 10:51

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተዘጋጀው አዲሱ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ፓኬጅ ዛሬ ይፋ ተደረገ፡፡ 


ፓኬጁ አሁን አገሪቱ የደረሰችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እና ዕድገት ከግምት በማስገባት እንደገና ከ14 ዓመታት በኋላ የተከለሰ ሲሆን ክለሳው ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ፈጅቷል፡፡


የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን የፓኬጁን ይፋ መሆን አስመልክተው እንደገለፁት ከ14 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ2005 ተዘጋጅቶ የነበረውን ፓኬጅ አዳዲስና ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ዘርፎችን በማካተት እንደገና ይፋ ሆኗል፡፡


ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች አሳክታ ከዚያም ወዲህ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለመተግበር ፊርማዋን ያኖረች ሀገር መሆኗን ሚኒስትሩ አስታውሰው ጤና ለሁሉም የሚለውን አገር አቀፍ የጤና መርህ ለማሳካትና ለህብረተሰቡ ተገቢውንና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ ታልሞ ፓኬጁ መዘጋጀቱን አብስረዋል፡፡


ከ14 ዓመት በፊት ተዘጋጅቶ የነበረው ፓኬጅ በሶስት ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር የገለፁት ዶ/ር አሚር አማን አዲሱ ፓኬጅ ግን በዘጠኝ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር በአጠቃላይ 1018 የጤና አገልግሎቶችን ማካተቱን ጠቅሰዋል፡፡


ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በቅንጅት የሚተገብሩትን የወረዳ ትራንስፎርሜሽንና ዕቅድን ያካተተው አዲሱ ፓኬጅ ከተለያዩ የጤናው ዘርፍ ኘሮግራሞች ጋር በመሆን በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ለሚዘጋጀው ሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋና ግብዓት እንደሚሆን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡


በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሚተገበረው ይሄው ፓኬጅ መንግስት በዘርፉ ለህብረተሰቡ የሚያሳየውን ግልፀኝነት የሚያረጋግጥበት እንደሆነና አገልግሎቱም በመንግስት ብቻ ሣይሆን በግሉም ዘርፍ የተሟላ እንዲሆን የፓኬጁ ሚና የጎላ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡


ሚኒስትሩ ለፓኬጁ ዝግጅት ተገቢውን ድጋፍና ጥረት ላደረጉት የአገር ውስጥና የዉጪ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል፡፡