ጤና ሚኒስቴር  ከ15 አመት በላይ የሚያገለግል የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም  ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት የሚያግዝ የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል‬

Submitted by dawit.berhanu on Tue, 11/12/2019 - 10:08

ከ14 አመት በፊት ትግበራ ላይ የዋለው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ላይ የተሰራው ‬ የጥናት ውጤቱ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ላይ ተጠናክረው መቀጠል የሚገባቸው  ጠንካራ ጎኖች ፣ መሻሻል የሚገባቸው እና መጨመር ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ጥናት መሆኑን የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን ተናግረዋል::


በጥናቱ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ያሉ ተዋረዶች የተሳተፊበት ሲሆን ከተገኘው ጥናት መነሻ በማድረግ ለሁለተኛ የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ  ዝግጅት አጋዥ ተደርጎም ይወሰዳል ብለዋል የጤና ሚኒስትሩ ፡፡


የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም ትግበራ በመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ፣በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በአከባቢ ጤና አጠባበቅና በሽታ መከላከል ላይ ያስገኘው  ውጤት በጥናቱ የተገለጸ  ሲሆን የጤና ኬላዎች ግንባታ ደረጃ፣ መብራት፣ ውሃ፣ በጤና ኬላዎች ደረጃ መገኘት ያለበት መድሃኒት መቆራረጥ እንዲሁም መረጃ አያያዝና ሪፖርት አደራረግ ክፍተቶች በጥናቱ በጥልቀት መዳሰሳቸውን በጤና ሚኒስቴር የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራምና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ዳሬክተር አቶ ተመስገን አየሁ ተናግረዋል፡፡


የጥናቱ ውጤት በቀጣይ አስራ አምስት አመት የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም እንዴት መመራት እንዳለበት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት የሚያግዝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር በሁሉም አካባቢዎች  የሚሰጡ አገልግሎት ተመሳሳይና ወጥ መሆን እንደሌለባቸውና በቀጣይ በምን መልክ መተግበር እንዳለበትም አመላካች መፍትሔዎችን    ጥናቱ ማካተቱን ጥናቱን ያከናወኑት ዶ/ር አሉላ መረሳ ተናግረዋል፡፡


ጥናቱ የተጠናው በመርክ ኮንሰልታንሲ፣ በቢል ኤንድ ሜሌንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እና በኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር ገለልተኛ  በሆኑ አካላት ነው፡፡