በተለያዩ የጤናው ዘርፍ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር የቆየው ገባኤ ተጠናቀቀ

Submitted by dawit.berhanu on Mon, 10/21/2019 - 10:05

በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በተለያዩ የጤናው ዘርፍ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር የቆየው 21ኛው ዓመታዊ ገባኤ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ፤ ከጤና ሚኒስቴር፤ ከተጠሪ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ በድምሩ ከ900 በላይ ተሳታፊዎችን ለአራት ቀናት ያስተናገደው ገባኤው በተለይም ባለፉት ሁለት ቀናት በቡድን ውይይት በመሳተፍ ለቀጣይ ስራ አጋዥ የሆኑ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡

በሰባት ቡድኖች ተከፋፍለው የተወያዩት ተሳታፊዎች በተለይ በወረዳ ትራንስፎርሜሽን፤በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የጥናት ውጤት፤ በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ፤በአዕምሮ ጤና፤ በቲቢ፤በቆላ በሽታዎች፤በክትባት፤ ያገባኛል /I-CARE/ እና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት ስንቅ የሚሆኑ ነጥቦች ተገኝተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚን አማን በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት በ2012 ዓ.ም 150 ወረዳዎች ትራንስፎርም እንዲያደርጉ ቃል መገባቱን አስታውሰው ሁሉም ክልሎች ለዚሁ ስኬት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ለሚከናወነው ዘርፈ ብዙ የጋራ ተግባርም በ100 ወረዳዎች ላይ እውን ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም በየቡድኖቹ የቀረቡትን ጠቃሚ ነጥቦች በማደራጀት በዌብሳይት ስለሚወጡ በቀጣይም የጤናውዘርፍ አባላት አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት አሳስበው ሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማዘጋጀት የሚደረገውን ጥረትና ተግባር በመነሻ ጥናትና በአዳዲስ አሰራሮች በሚገባ ተፈትሾ መከናወን ይገባዋል ብለዋል፡፡

በጤና ኤክስቴንሽን ቀጣይ ሂደት ላይ የተጀመሩ ስራዎች አዲስ እየተዘጋጀ ባለው ፍኖተ ካርታ በጥልቀት እንደሚፈተሸ ጠቁመው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና ለስራው ትኩረት ሰጥቶ በኃላፊነት ስራውን እንደሚከታተል ገልጸዋል፡፡

በማጠቃለያው የአራማውር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት 50ኛ ዓመት የምስረታ ቀን በማስመልከት የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ገነቱ ለተሳታፊዎቹ አጠር ያለ ገለጻ አድርገው የበዓሉ አከባበር በቀጣይ ጊዜያት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የጤና ሚኒስቴር ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የጤና ቢሮዎች ጋር የ2012 ዓ.ም የጤናው ዘርፍ ተግባራትን በተመለከተ የቃል ኪዳን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በመጨረሻም ባለአስር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማቅረብና በቀጣይ የ22ኛውን የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ አዘጋጅ የጅግጅጋ ከተማ እንድትሆን በመወሰን 21ኛው ጉባኤ ተጠናቋል፡፡