21ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀመረ

Submitted by zelalem.worku on Wed, 10/16/2019 - 11:24

የጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 21ኛው የጤናው ዘርፍ  ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተጀመረ፡፡

 "ዘርፈ ብዙ ትብብር - ለጤናማና የበለጸገች ሃገር" በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን ጉባኤ በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ጤናና ጤንነት የፈጣሪ መልካም ጸጋዎች ናቸው ካሉ በኋላ ጤናማና ምርታማ ዜጋ ለማፍራት በተደረገው እንቅስቃሴ ለተሰማራችሁት ባለሙያዎች በሙሉ በዚህ አጋጣሚ ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በበኩላቸው ለጉባኤተኞቹ ባሰሙት መልእክት በጤናው ዘርፍ በሁሉም አቅጣጫ ለተመዘገቡት ድሎች ዋነኛ ተዋናይ ለሆኑት ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና በዘርፉ ለተሰማሩት ጤና ሙያተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የ2011 በጀት ዓመት ዋና ዋና አፈጻጸሞችን ለታዳሚው በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በተለይም በሰለጠነ ባለሙያ የወሊድ አገልግሎት እኤአ በ2016 28 በመቶ የነበረው በ2019 ወደ 50 በመቶ አድጓል ብለዋል፡፡

በአራቱ የአርብቶ አደር ክልሎችና በሰባት ዞኖች ላይ ፍትሃዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት በተደረገው ጥረትም መልካም ውጤቶች መመዝገባቻን አውስተው ከ300ሺ በላይ የሚሆኑ አባወራዎችንና እማወራዎችን የቤተሰብ ጤና መረጃ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ መመዝገቡን ዶ/ር አሚር አስታውቀዋል፡፡

በዕለቱ በጤናው ዘርፍ ለላቀ የሙያ አገልግሎት፣ በስራ ሃላፊነት የላቀ አገልግሎት፣ በሙያ መስክ የላቀ ልዩ ስራና አገልግሎት፣ በግሉ ዘርፍ የላቀ ልዩ ስራ አገልግሎት እና በጤና ኤክስቴንሽን የላቀ የሙያ አገልግሎት የተመረጡ ባለሙያዎች ሽልማታቸውን ከዕለቱ የክብር እንግዶች ተቀብለዋል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የፖሊስ ሰራዊት የማርሽ ቡድን እና የአዲስ አበባ ህጻናትና ወጣቶች የቲያትር አባላት ጣዕመ ዜማዎችንና ትምህርታዊ ድራማ ያቀረቡ ሲሆን ጤና ሚኒስቴር፣ ክልሎች፣ ተጠሪ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች ያዘጋጁት አውደ ርዕይ በክብር እንግዶችና በጉባኤው ተሳታፊዎች ተጎብኝቷል፡፡