7ኛው ብሄራዊ የጤና ወጪ ስሌት የጥናት ውጤት ይፋ ሆነ

Submitted by dawit.berhanu on Fri, 09/20/2019 - 16:56

ብሄራዊ የጤና ወጪ ስሌት የጥናት ውጤት በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል። ይፋ በተደረገው የጥናት ውጤት መሰረትም አጠቃላይ የጤና ዘርፍ ወጪ በ2006 ዓ.ም ከነበረው 49 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በ2009 ዓ.ም ወደ 72 ቢሊየን ብር ከፍ ብሏል።

ለህክምና ከታካሚዎች ኪስ የሚወጣ ውጪ ደግሞ ከ33 በመቶ ወደ 31 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፥ ከመንግስት የሚወጣው ወጪ ደግሞ ከ30 በመቶ ወደ 32 በመቶ ከፍ ብሏል። 2009 ላይ የታካሚዎች የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ 33 ነጥብ 22 የአሜሪካ ዶላር መድረሱ በጥናቱ ተመላክቷል።

ከአጠቃላይ የጤና በጀት 41 በመቶ የሚሆነው የሚውለው በመጀመሪያ ደረጃ የጤና አጠባበቅ ክፍል ሲሆን፥ 29 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በሆስፒታሎች ደረጃ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ለጤናው ዘርፍ የሚመደበውን በጀት በተለይም የሀገር ውስጥ ፋይናንስ ማሳደግ፣ የበጀት ድልድል እና የሆስፒታሎች ወጪ መተኪያ ሞዴል መቅረፅ በጥናቱ የተመለከቱ የወደፊት አቅጣጫዎች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ተናግረዋል።

ብሄራዊ የጤና ወጪ ስሌት በሀገር አቀፍ ደረጃ በየሶስት አመቱ የሚሰራ ስሌት ነው።