የሕሙማን ደህንነት የዓለም ቀዳሚ የጤና ጉዳይ

Submitted by dawit.berhanu on Fri, 09/20/2019 - 16:33

የዓለም የህሙማን ደህንነት ቀን አከባበር በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረበት ዕለት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንዳሉት የዓለም የጤና ድርጅት በነበረው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የዓለም አገራት የችግሩን አሳሳቢነትና በጤና ተቋማት ውስጥ ያለው የህሙማን ደህንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ችግር እየሆነ እንደመጣ ገልጸው አገራቱ በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ የህሙማን ደህንነት ቀን እንዲከበርና ግንዛቤ እንዲፈጠር በተስማሙት መሰረት በዓለምም በአገራችንም ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ዶ/ር ሊያ አያይዘውም በዓለም ደረጃ ከ13 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህሙማን ደህንነታቸው ባለመጠበቁ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸውና ከነዚህም ውስጥ 2.6 ሚሊየን የሚሆኑት ህሙማን እንደሚሞቱ ጨምረው አብራርተው በየሆስፒታሉ የህሙማንን ደህንነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የህሙማኑን ደህንነት መጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተግባር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ያዕቆብ ሰማን በበኩላቸው እንደተናገሩት የጤና ሚኒስቴር የህሙማን ደህንነትን ለማስጠበቅ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ንጹህ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ ሆስፒታሎች እንዲኖር ከማድረግ አንጻር የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት በተባለ እንቅስቃሴ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩና ደህንነቱ የተጠበቀ ህክምና ህይወት ያድናል በሚል ትግበራ ደግሞ የቀዶ ህክምና አሰራር ስርዓት ደህንነት ማሻሻል የተቻለ መሆኑን እንዲሁም የመድሃኒት ደህንነትን ለማስጠበቅ ደግሞ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በዝግጀቱ ላይ የዓለም ጤና ድርጀት በኢትዮጵያ ተወካይ ተገኝተው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፕሮግራሙም በፓናል ውይይትና በሆስፒታሎች ጧፍ በማብራት የህሙማን ደህንነትን ቀዳሚ የጤና ጉዳይ እንዲሆን ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ተከብሮ ውሏል ፡፡