መለስተኛ የስነ-ሕዝብ እና ጤና አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ዋና ዋና ጠቋሚ መረጃዎች ይፋ ተደረጉ

Submitted by dawit.berhanu on Wed, 08/28/2019 - 15:24

የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ እና የተሻለ የጤና አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመቀየስ የሚያስችል መለስተኛ የስነ-ሕዝብ የጤና ዳሰሳ ጥናት ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ወራት ሲያካሄድ ቆይቶ ዋና ዋና የጥናቱ ጠቋሚ መረጃዎችን  በጤናው ዘርፍ ለተሰማሩ አጋር ድርጅቶች ይፋ አደረገ፡፡


ጥናቱ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በአገር-አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 305 የቆጠራ ጣቢያዎች የተካሄደ ሲሆን በ8,663 አባወራዎች ቤት እድሚያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ማለትም በመዉለድ የዕድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ 8,885 ሴቶች ላይ የጥናቱን መረጃ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ለክትባት መረጃ ዕድሚያቸው ከ2 እስከ 3 ዓመት የሆናቸው 1,028 ህጻናት  እንዲሁም ለቁመትና ክብደት ልኬት ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 4,990 ልጆች በጥናቱ ተካተዋል፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት የተካሄደውን የስነ-ሕዝብ የጤና ዳሰሳ ጥናት ምስል 1 ላይ ባለው ሰንጠረዥ በንጽጽር ቀርቧል፡፡

Table
ከላይ በሰንጠረዡ እንደሚታየው በ2011 ዓ.ም ወይም እ.ኤ.አ በ2019 የተካሄደው የስ-ሕዝብ ጤና የዳሰሳ ጥናት ውጤት በንጽጽር ሲታይ ቀደም ሲሉ ከተካሄዱት መሰል ጥናቶች በጤናው ዘርፍ ያለው የጤና አገልግሎት እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ያስችላል፡፡ 
ይህ መለስተኛ የስነ-ሕዝብ እና የጤና ዳሰሳ ጥናት በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት እና በኢትዮጵያ የህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩትና በተለያዩ የጤና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር  የተካሄደ ሲሆን የዓለም ባንክ ፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ዩኒሴፍ ቴክኒክና የበጀት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ዋና ዋና የጥናቱ ጠቋሚ መረጃዎችን  በጤናው ዘርፍ ለተሰማሩ አጋር ድርጅቶች ይፋ ተደርጎ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከውይይቱ የተገኙ ነጥቦችም በቀጣይ በዘርፉ ለሚሰሩ ስራዎች ግብዓት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡