የዘርፈ ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን የሙከራ ትግበራ በጊምብቹ ወረዳ ሊጀመር ነው፡፡

Submitted by dawit.berhanu on Mon, 08/12/2019 - 19:20

የዘርፈ-ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን /Multi-sectoral Woreda Transformation/ የሙከራ ትግበራ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምብቹ ወረዳ ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ፡፡

አስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት ይህ የዘርፈ-ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን የሙከራ ትግበራ ከመስከረም 1 እስከ የካቲት 30/2012 ዓ.ም ድረስ ለ6 ወራት የሚተገበር ይሆናል፡፡ የዘርፈ-ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን የሙከራ ትግበራውን ልኬት ማስቀመጥ እንዲቻልም አጠቃላይ የወረዳው ነባራዊ ሁኔታ መረጃ ዳሰሳ ስራ /Baseline Data Assessment/ የሚሰራ ሲሆን ለዚህም ስራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በጊምብቹ ከተማ በተዘጋጀው ይፋዊ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን እንደተናገሩት በ6 ወራት የሙከራ ትግበራ ወቅት ውጤት ለማስመዝገብ ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው በጊምብቹ ወረዳ የዘርፈ-ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን የሙከራ ትግበራ ስራ ቤተሰብን ማዕከል በማድረግ ወደ ቀበሌና ወረዳ የሚሸጋገር መሆኑን ጠቅሰው በጊምብቹ ወረዳ የሚገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግም ወደ ሌሎች የሃገራችን ወረዳዎች እንዲሸጋገር በማድረግ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ እኩል ተጠቃሚ የሆነ ህብረተሰብ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጊምብቹ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደመወዜ ወዳጀነው በበኩላቸው በዘርፈ-ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን የሙከራ ትግበራ ወረዳቸው በመመረጡ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረው ትግበራውም በስኬት እንዲጠናቀቅ የወረዳው አመራርና ህብረተሰብ ተባብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የዘርፈ-ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ሴክተር መ/ቤቶች በወረዳ ትራንስፎርሜሽን የያዙትን ግቦች ለማሳካት በተናጥል ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ ያላቸውን ሃብት በማቀናጀትና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ የህብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግር በቅደም ተከተል በመፍታት አንዱ ችግር ሲፈታ ሌሎችም አብረው እየተፈቱ የሚሄዱበትን ስርዓት ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ነው፡፡