የጤናው ዘርፍ የህዝብ ግንኙነትና ጤና ኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ የ2011 ዓ.ም ዓመታዊ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2012 ዓ.ም ዕቅድ ገለጻ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

Submitted by dawit.berhanu on Thu, 08/08/2019 - 10:50

በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙትን ግቦች ለማሳካት የዘርፉ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ተገለጸ፡፡


ይህ የተገለጸው የጤናው ዘርፍ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኔትወርክ በሐረር ከተማ የ2011 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2012 የሥራ ዕቅድ ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ መክፈቻ ላይ ነው፡፡ ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ የኔትወርኩ አባላት የ2011 ዓ.ም ሥራ ዕቅድ አፈጻጸማቸው የሚገመገም ሲሆን የ2012 የበጀት ዓመት ሥራ ዕቅድ በማቅረብ የሚወያዩበት ይሆናል፡፡


ይህንን የግምገማ መድረክ በንግግር የከፈቱት የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኢብሣ ኢብራሒም እንደተናገሩት ኔትወርኩ ከአዲስ አበባ እና ከአዳማ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ የሐረር ከተማ እንድታስተናግድ ዕድል በማግኘቷ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በ2012 በሚጠናቀቀው ሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙትን ግቦች ለማሳካት የዘርፉ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና ከፍ ያለ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጤናው ሴክተር አመራሮችም ይህንን ተገንዝበው ከሌላው ጊዜ የበለጠ አብረው እየሠሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡


የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ም/ዳይሬክተር አቶ ዮርዳኖስ አለባቸው በበኩላቸው እንደገለጹት የኅብረተሰቡን ንቃተ ጤና ለማሳደግ የኔትወርኩ አባላት የሆኑት የዘርፉ ባለሙያዎች ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው አሁንም በጋራ የሚታቀዱ ዕቅዶችን ከዳር ለማድረስ የጋራ ጥረት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ለአራት ቀናት ከሚቆየው ከዚህ የግምገማ መርሐግብር ጎን ለጎን የውይይቱ ተሳታፊዎች የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮን የወረዳ ትራንስፎርሜሽን አተገባበር ለመቃኘት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡


የጤናው ዘርፍ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ኔትወርክ የፌደራል ጤና ሚኒስቴር፣ የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት እና የሪፈራል ሆስፒታል ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን ያቀፈ ነው፡፡