የቤተሰብ ጤና መመሪው  ልዩ ትኩረት ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚመች መልኩ ተዘጋጀ

Submitted by dawit.berhanu on Fri, 07/19/2019 - 17:16

የቤተሰብ ጤና መመሪው  ልዩ ትኩረት ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚመች መልኩ ተዘጋጀ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ እንዲዳረስ የሚለውን መርህ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንን መርህ ለማሳካት የጤና ሚኒስቴር ከ4ቱ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች አንዱ በሆነው ፍትሃዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሁሉም ለማዳረስ የሚለውን አጀንዳ ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡  ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋናው ልዩ ትኩረት ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ፍትሃዊና ጥራት ባለው መልኩ እንዲዳረስ ማድረግ ነው፡፡

በ2011 እ.አ.አ በተደረገው የዓለም ጤና ድርጅት እና የዓለም ባንክ ባወጡት ሪፖርት መሰረት በሀገራችን 15 ሚሊየን የሚጠጉ የአካል እንቅስቃሴ ጉዳት ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ይኖራሉ:፡ 4 ሚሊየን የሚሆኑ ዓይነ ስውራንዝቅተኛ ዕይታ ያላቸውን ጨምሮ እንደሚኖሩ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

የጤና ሚኒሰቴር ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትና መጠነኛ ዳሰሳዊ ጥናት በማካሄድ ለዓይነ ስውራን እና መስማት ለተሳናቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ምን  አይነት የጤና አጠባበቅ ትምህርት መርጃ መሳሪያ እንደሚያሰፈልጋቸው  ልየታ አካሂዷል፡፡ በዚህም መሰረት የተለያዩ የጤና መረጃ ክፍተቶች የተለዩ ሲሆን ከነዚህም  መካከል   የቤተሰብ እቅድ፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ቲቢ፣ የሃይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ፣ ተላላፊ ተላላፊ ያልሆኑ  በሽታዎች፣ የስነ ተዋልዶ ጤና  እና የመሳሰሉት የጤና ችግሮች መኖራቸው ተስተውሏል፡፡

በዚህም መሰረት የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ቁልፍ መልዕክቶችን የያዘውን  የከተማ የቤተሰብ ጤና መመርያ ለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች  በሚመች መልኩ  ማለትም  ለዓይነ ስውራን  በድምፅ (ኦዲዮ ፎርማት) እና በብሬይል እንዲሁም  መስማት ለተሳናቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በምልክት ቋንቋቸው በምስል ወድምፅ (ቪዲዮ ፎርማት) አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መርጃ መሳሪያዎች  በህትመት፣ በሲዲ እና በፍላሽ ዲስክ  በማባዛት በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ማህበራት፣ ጤና ተቋማት፣ ላይብረሪዎች እና ትምህርት ቤቶች በማሰራጨት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የሚሆን ይሆናል፡፡   

በተጨማሪም የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ይህንኑ ቁልፍ መልዕክት የያዘ መመርያ ለsmart phone የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች በተለይም ለወጣቶች፣ ለእናቶች፣ የአካል እንቅስቃሴ ጉዳት ላለባቸው ፣ እና ለመላ ቤተሰብ የሚሆን የሞባይል መተግበሪያ አዘጋጅቷል፡፡ በ2018 እ.አ.አ የኢትዮ ቴሌኮም ሪፖርት መሰረት በሀገራችን 40.4 ሚሊየን የሞባይል ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ 12.7 ሚሊየን የሚሆኑት smartphone ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

ሰለሆነም የጤና ሚኒስቴር ይህንን የሞባይል መተግበሪያ የተለያዩ የማሰራጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ማህበረሰቡ አዎንታዊ የጤና ባህርያትን እንዲያዳብርና የራሱን ጤና በራሱ ማምረት እንዲችል እንዲሁም የጤና አገልግሎትን እንዲጠቀም ያስችላል፡፡   

ስለሆነም ይህን ተግባር የበለጠ ለማጠናከርና ለማስፋፋት ይቻል ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና አጋር አካላት እንዲሁም የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ ይወጡ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ሁሉ ስራ ስኬት ከጎናችን የነበሩትን በበጎ ፍቃደኝነት የኦዲዮ እና የቪዲዮ ስራዎችን በነፃ የሰሩልንን የኢሳግ ፊልም ፕሮዳክሽን ባለቤት አቶ ኢሳያስ፣ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሄራዊ ማህበርን፣ የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበርን እና  JSI(AIDS Free Project)ን፣ ለማመስገን እወዳለሁ ፡፡

ተጨማሪ መረጃ ከፈለጉ፡-

አዳኑ ዘውዱን በ 09-11-66-89-08

የውብዳር ሂርጻ 09-20-38-29-86