"እኔ እጄን በአግባቡ እታጠባለሁ ሕይወትም አድናለሁ!" በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚቆይ እጅ የመታጠብ ንቅናቄ በይፋ ተጀመረ።

Submitted by admins on Fri, 10/16/2020 - 09:59

ለአንድ ወር የሚቆየው እጅ የመታጠብ ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ሰው እጁን በአግባቡ በመታጠብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ንቅናቄውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ እጅን መታጠብ የሚያስገኘውን የጤና ጠቀሜታ በመረዳት ከእጅ ንጽህና ጉድለት የተነሳ ከሚመጡ በሽታዎች እራሳችንን መከላከል ይጠበቅብናል ያሉ ሲሆን በይበልጥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እጅን በአግባቡ መታጠብ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ለመከላከል የሚኖረውን ጠቀሜታ በመረዳት የአለም ጤና ድርጅት በሚመክረው መንገድ ለሃያ ሰከንድ እጅን በሳሙና በአግባቡ መታጠብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የኮረና ቫይረስ የላቦራቶሪ መመርመርያ ኪት ማምረቻ ፋብሪካ ተመረቀ::

Submitted by admins on Wed, 09/16/2020 - 09:46

በኢትዮጵያ መንግስትና በቻይናው ቢጂአይ ሄልዝ ትብብር የተቋቋመው ፋብሪካ ዛሬ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የፋብሪካው መገንባት በአፍሪካ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን የመመርመር አቅም በማሳደግ የተሻለ የመከላከል ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ ተናግረው ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ካሞላች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እክስፖርት በማድረግ እንደአህጉር በሽታውን የመከላከልን ተግባር ታግዛለች ብለዋል።

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፖርክ የተገነባው ፋብሪካ በዓመት 10 ሚሊየን ኪቶችን እንደሚያመርት የተገለጸ ሲሆን ኮረና ከጠፋ በኋላ የኤች አይቭ እና ቲቢ የላቦራቶሪ መመርመርያ ኪቶችን የሚያመርት ይሆናል።

የአዲስ አበባ የኮቪድ-19 የፊልድ ሆስፒታል ስራ ጀመረ።

Submitted by admins on Wed, 09/16/2020 - 09:44

በቦሌ ቡልቡላ አከባቢ በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በአለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፍ የተገነባው የአዲስ አበባ የኮቪድ-19 የፊልድ ሆስፒታል ስራ ጀምረዋል።

ሆስፒታሉን በይፋ ስራ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሆስፒታሉን ለመገንባት ድጋፍ ላደረገው የአለም ምግብ ፕሮግራም እና ሆስፒታሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ስራ እንዲጀምር የቅርብ ክትትል በማድረግ አመራር የስጡትን አካላት በሙሉ አመስግነዋል።

ሆስፒታሉ በተለይም በኮሮና በሽታ ተይዞ የጸና የህመም ምልክት ለሚያሳዩ ህሙማን የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን አስፈላጊ የሆኑ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ተሟልቶለታል።

ምክትል ጠቅለይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአዲስ አበባ ኮቪድ 19 ፊልድ ሆስፒታልን ጎበኙ

Submitted by admins on Sat, 08/29/2020 - 17:34

ምክ/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና ሌሎች የኮቪድ 19 ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አከባቢ ለኮቪድ 19 የጸና ህመም ምልክት ለሚያሳዩ ህሙማን የህክምና አገልግሎት እየተዘጋጀ ያለውን የአዲስ አበባ ኮቪድ 19 ፊልድ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።

የአዲስ አበባ ኮቪድ 19 ፊልድ ሆስፒታል በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በአለም ምግብ ፕሮግራም ድጋፍ የተሰራ ነው። ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመር የጤና ሚኒስቴር፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የአለም ጤና ድርጅት አስፈላጊውን የሰው ኃይልና ሌሎች ዝግጅቶች እያደረጉ ይገኛሉ። በዚሁ መሰረት የፊታችን ጳጉሜ 5 ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ታምሩ አስፋ ተናግረዋል። ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር 200 አልጋ ይኖረዋል::

ጤና ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደገም ወረዳ የችግኝ ተከላና ጉብኝት አካሂዷል።

Submitted by admins on Fri, 08/28/2020 - 12:22

ጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት እና ከአከባቢው ነዋሪዋች ጋር በመሆን በደገም ወረዳ በአረንጓዴ አሻራ የመዝግያ ዝግጅት ላይ ከ50ሺ በላይ ችግኞች መተከላቸውን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን በዘንድሮ የክረምት ወራት የኮሮና ቫይረስን እየተከላከለ ከ500 መቶ ሺ በላይ ችግኞች መተከሉን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

ከችግኝ ተከላው በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የደገም ጤና ጣቢያ፡ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፤ የፍቼ ጠቅላላ ሆስፒታል እና የሙከ ጡሪ የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከልት የተጎበኙ ሲሆን ጤና ተቋማቱ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ከፍ ለማድረግ ጤና ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ያለባቸው ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

በተጎበኙ የህክምና ተቋማት ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራ የማስቀመጥ ስራ ተከናውኗል ።