ጋዜጣዊ መግለጫ

አሁን ላይ በአገራችን እየተሰጠ ያለውን የኮቪድ 19 ክትባት እና በቀጣይ በሚሰጠው 2ኛ ዙር ክትባት መርሃ ግብር ዙሪያ ከጤና  ሚኒስቴር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ


እንደሚታወቀው አሁን ላይ አገራችንን ጨምሮ የአለም አገራት አስከፊውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተዋጉ ዜጎቻቸውንም ከወረርሽኙ ለመጠበቅ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በሀገራችን ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተወሰዱት ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች ብዙ ውጤት ያመጡ ቢሆኑም ወረርሽኙ ግን አሁንም የህዝባችን የጤና ስጋት ሁኖ ቀጥሏል፡፡ በአገራችን እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስም 274,346 ያክል ወገኖቻን ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋ፤ 4,250 ያህል ወገኖቻችን በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡


ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በሙሉ አቅም ከመተግበር እና ከማስተግበር ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግስት ኮቫክስ ከተሰኘ አለም አቀፍ ጥምረት 2.2 ሚሊዮን የሚጠጋ ክትባት በወርሃ የካቲት 28/2013 ዓ.ም ተረክቦ የጤና ሚኒስቴርም ክትባቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የህረተሰብ ክፍሎች ለይቶ የክትባት መስጠት መርሃ ግብሩ በተቀናጀና በታቀደው መሰረት በሁሉም ክልልሎችና ከተማ መስተዳደሮች አከናውኗል፡፡ 


ከዚህም አንፃር የመጀመሪያውን ክትባት ለተጠቃሚዎች በማዳረስ ረገድ አፈፃፀሙ ከክልል ክልል የተወሰነ ልዩነት ቢኖረውም በአገር አቀፍ ድረጃ አገር ውስጥ ከገባው የክትባት መጠን ውስጥ ከ 94% በላይ ክትባቱ ያስከትላል ተብለው ሲነገሩ የነበሩ ኢ- ሳይንሳዊ ጉዳቶች  ሳይከሰቱ የሚጠበቁት የጎኑዮሽ ስሜቶችን በተወሰኑ ሰዎች በማስተናገድ መፈፀም ተችሏል:: ይህ የክትባት አፈፃፀም ኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ቀዳሚ ያደርጋታል፡፡ 


ይህ በእንዲህ እንዳለ ህንድ ውስጥ በተከሰተው ያልተጠበቀ አስከፊ የወረርሽኙ ገፀታ ምክንያት ህንድ የሚገኝው ሴረም እንስቲቲዩት ኦፍ ኢንዲያ የተባለው ግዙፉ የክትባት አምራች ኩባንያ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አጠቃላይ ምርቱን ለአገር ውስጥ ፍጆታ በማዋሉ ኮቫክስ በተባለው የአለም አቀፍ የክትባት ትስስር ለታዳጊ ሀገራት ሊስራጭ የታሰብው ሁለትኛው ዙር የኮቪድ 19 ክትባት ሊዘገይ እንዲሁም በአጠቃላይ ከፍተኛ የክትባት እጥረት ሊከሰት ችሏል::


ይህም ችግር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉንም በማደግ ላይ ያሉትን አገሮችን የሚነካ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት፤ የጤና ሚኒስቴር ሁሉንም ዓይነት ቅንጅታዊ ጥረት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በመስራት ላይ ይገኛል::  

 

  1. የአለም  የጤና ድርጅት ከተፈጠረው  ችግር ጋር ተያይዞ በቅርቡ ያወጣውን መመሪያ እና ምክረ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ጤና ሚኒስቴር ቀደም ሲል  የመጣውን 2.2 ሚሊዩን ክትባት ለህብረተሰቡ በመጀመሪያ ዙር በማዳረስና በመከተብ አጠቃላይ በማህበረሰብ ደረጃ ከክትባቱ የሚገኝውን ጥቅም ማለትም ወረርሽኙን መቀነስ በፅኑ መታመምን ሞትን ጨምሮ መቀነስ ስለሚቻ፣ ይህንን አጠናክረን እየሰራን ሲሆን ከዚያ ጎን ለጎን፤  
  2. መንግስት ለኮቪድ 19 ክትባት ግዢ ሊውል የሚችል ተጨማሪ ፋይናንስን በመመደብ የኮቪድ 19 ክትባትን በአይነትም በመጠንም ለመጨመር ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከአፍሪካ ሕብረት ጋር እየሰራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የጤና ሚኒስቴር አስትራዜኒካ እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባሉ ክትባቶችን ለመግዛት የግዢ ሂደቶችን የጀመረ  ሲሆን የዚህን ሂደት እና ውጤት ለማህበረሰቡ በየጊዜው የሚያሳውቅ ይሆናል ፡፡
  3. የጤና ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለ ድርሻ  አካላቶች ጋር በመሆን ተጨማሪ ክትባቶችን ከለጋሽ አገሮችና እና ክትባትን ከሚያመርቱ ተቋማት ለማግኝት ሰፊ ስራ እየተሰራ ሲሆን ቀደም ሲልም ከቻይና መንግስት የተገኝው 300 ሺ የሳይኖ ፋርም ክትባት የዚህ ስራ ውጤት ነው፡፡  ይህም ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ተጨማሪ ክትባቶችን ለማግኝት የጤና ሚኒስተር በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አማካኝነት በየአገሩ ካሉ የቆንፁላ ጽ/ቤቶች፣ ጋር በመሆን መጠነ ሰፊ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል:: 
  4. ሌላው በመንግስት በኩል ትኩረት የተሰጠው የኮቪድ-19 ክትባቶችን በአገር ውስጥ ማምረት ሲሆን ሌሎች ሀገራት አገር ውስጥ ካሉ የግል የፋርማሲትካል እንዳስትሪዎች ጋር በመተባበርና አስፈላጊውን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በአጭር ግዜ ውስጥ የኮቪድ 19 ክትባትን በአገር ውስጥ እንዲመረት ለማስቻል እንቅስቃሴዎች ጀምረናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት ቻይና ከሚገኝ የክትባት ተቋም ጋር በትብብር በመስራት ላይ ሲሆን በቅርቡ አጠቃላይ የትብብር ስምምነት ምዕራፉ ተጠናቆ ወደ ተግበራዊ እንቅስቃሴ  እንገባለን  ብለን እናምናለን::


ከላይ በዘረዘርኳቸው  ቅንጅታዊ  ጥረቶች መሰረትም በቅርቡ በተለያየ መጠን ተጨማሪ ክትባት መምጣት እንደሚጀምር ከኮቫክስ የዓለም አቀፍ ጥምረት የተገለጸልን ሲሆን ይህን   ከግምት ውስጥ በማስገባት እና የዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብን ታሳቢ በማድረግ የሁለተኛው ዙር የኮቪድ 19 ክትባት  እንደመጀመርያው ዙር የክትባት አሰጣጥ መርሃ ግብር ሁሉ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደረጃ በደረጃ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ 


በዚህ መሰረት ቀደም ሲል በመጀመርያ ዙር  በስራቸው ምክንያት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑና እና በበሸታው ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችሉ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች ቅድሚያ በመስጠት ሁለተኛው ዙር ክትባት የሚሰጥ ይሆናል::  

 

  • የአስትራዜኒካ ክትባት ሁለተኛው ዶዝ ከ2 ወር እስከ አራት ወር ባለው ወራት የሚሰጥ በመሆኑ፣ የመጀመሪያ ዙር የወሰዱ እና ክትባቱን ከወሰዱ (ሦስት) ወራት የሞላቸው የጤና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ሁለተኛው ዙር የኮቪድ 19 ክትባት በመጀመሪያ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡
  • በቀጣይም ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት 3 ወር ለሞላቸዉ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ደረጃ በደረጃ ክትባቱ የሚሰጥ ሲሆን ይህንንም በየጊዜው ለህብረተሰባችን የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

የኮቪድ 19 ክትባት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና በወረርሽኝ መልክ  ሊከሰት የሚችለውን ሞት እና ፀኑ ህመምን ለመቀነስ የሚያግዝ ነው፡፡ በዚህም አስካሁን ባደረግነዉ ጥረት ማለትም በክትባት አቅርቦት፣ በስርጨት፣ ክትባቱን በመስጠት፣ ተገቢዉን መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስ በኩል ሀሃሳብና ድጋፍ በመስጠት ለተሳተፋችሁ ሁሉ ምስጋናዬን እያቀረብኩ አሁንም ኮቪድ-19ኝን የመከላከል ስራ የሁሉንም ተቋማት ቅንጅታዊ ስራ የሚፈልግ በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል፣ ባለድርሻ አካላት፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ላይ እንድናደርግ መልዕክቴን እና ጥርዬን ከአደራ ጭምር  ለማስተላለፍ እወዳለሁ!

አመሰግናለሁ!
ጤና ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ

ሰኔ 2013 ዓ.ም
 

Amharic