Press Release Press Release

የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ወረርሽኝ መከላከልን  አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ባለፈው ሳምንት የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን አስመልክቶ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የመከላከያ ዘዴዎችን አስመልክቶ መግለጫ መሰጠታችን ይታወሳል፡፡ የዚህ ሳምንት መግለጫችን የሚያተኩረው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ለመከላከል የሚረዱ ከሕብረተሰባችን ጋር በጋራ መስራት ስለሚገቡን ተግባረት ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡     

  ይኸውም በአሁኑ ወቅት የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ወረርሽኝ በአፋር ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንደገና መቀስቀሱን ተከትሎ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከክልሉ ጤና ቢሮ እና አጋር ድርጅቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ  ምላሽ እየተሰጠ ሲሆን ይህም በሰብአዊ ሕይዎት ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን ጉዳት መቀነስ አስችሏል፡፡

የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ በአካባቢ እና በግል ንጽህና ጉደለት፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግር የሚከሰት በመሆኑ እና በቀላሉ ተላላፊ ስለሆነ ከሰዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ወደ ሌሎች አካባቢዎችና ክልሎች ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል፡፡ ከነዚህ ስጋቶች በተጫማሪም ከሌሎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ወረርሽኞች ካሉባቸው ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ባረፉባቸው ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎችና የቤተሰብ ወይም የጓደኛ ቤት ውስጥ እያሉ አጣዳፊ የሆነ ተቅማጥ ወይም ተቅማጥና ትውከት ምልክት ከታየባቸው በሽታው  ወደ ሌሎች ሰዎች  በቀላሉ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በመሆኑም የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ወረርሽኞችን ወደ ሌሎች ሰዎችና አካባቢዎች ሳይተላለፍ ለመከላከል እንዲቻል ከሆቴሎች፣ ከፔንሲዮኖች፣ ከቤተሰብ አባላት፣ ከትራንስፖርት ስጭ ግለሰቦች፣ ከጤና ተቋማትና ሕብረተሰቡ የሚከተሉትን የመከላከል ስራዎችን በከፍተኛ ኃላፊነት  ማከናዎን የሚገባቸው ይሆናል፡፡

 1. ሕብረተሰቡ፣ የትራንስፖርት፣  የመኝታ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችና ተቋማት/ ሆቴሎች፡
 • በተቅማጥ ወይም ትዉከት በሽታ የታመመ ደንበኛ ሲያጋጥም ወዲያውኑ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የመንግስት ጤና ተቋም መውሰድ/ሪፖርት ማድረግ፣
 • እንግዳው የተገለገለባቸውን አንሶላ፣ የአልጋ ልብስ፣ ምንጣፍ እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች በበረኪና ዘፍዝፎ ማጠብ፣
 • ከተቅማጥና ትውከት ጋር ንክኪ ያደረገ ወለል ወይም ተሸከርካሪ በረኪና አፍስሶ በሚገባ ማጽዳት፣
 • የታማሚውን ተቅማጥና ትውከት በፖፖ ወይም በሌላ እቃ በመቀበል መጸዳጃ ቤት ውስጥ ማፍሰስ፣
 • ለታማሚው ሰው እንክብካቤ ከሰጠን በኋላ እጃችንን በሚገባ በሳሙናና ውሃ መታጠብ፣
 • ምግብ ከማዘጋጀት፣ ከማቅረብ፣ ከመመገብ በፊት፣ ከመፀዳጃ ቤት መልስ እና ሕፃናትን ካፀዳዱ በኋላ እጅን በሳሙናና ውሃ በሚገባ መታጠብ፣
 • ማንኛውም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም/ግለሰብ፡ አጣዳፊ ተቅማትና ትውከት የሚመስል ታማሚ ሲያጋጥም ቶሎ በአቅራቢያው ወዳለ የጤና ተቋም በመውሰድ ታማሚውን ማድረስና ንክኪ ያደረገውን የተሸከርካሪ አካል ክሎሪን ማስረጨት ወይም በረኪና አፍስሶ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ማጠብ፣
 • ምግብን በሚገባ አብስሎ በመመገብ፣ ከድኖ እና በንጹህ ቦታ በማስቀመጥ ከዝንቦችና ከሌሎች ነፍሳት ንክኪ በመጠበቅ ራስንና ቤተሰብን ከተላላፊ በሽታዎች መከላከል ይጠበቅባቸዋል፡፡
 1. የጤና ተቋማት፡
 • ታማሚ ግለሰቦች ወደ ተቋማቱ እንደደረሱ ትራንስፖርት የሠጡ ተሸከርካሪዎችን ክሎሪን እንዲረጩ ማድረግ፣
 • የታማሚውን ሰው ልብስና ጫማ  በክሎሪን በሚገባ ዘፍዝፎ ማድረቅ፣
 • ታማሚው ሰው የተኛበትን ክፍል ርጭት ማሄድና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች መለየት፣ ክትትል ማድረግና እና ማስተማር፣
 • ሌሎች አጋላጭ ሁኔታዎችን በመለየት የእርምት እርምጃ መውሰድ፣
 • የግል የጤና ተቋማት እንደነዚህ አይነት ህሙማን ሲያጋጥም አስፈላጊውን የመጀመር እርዳታ በመስጠትና ተገቢውን መረጃ በማሰባሰብ ወደ መንግስት ተቋም ሪፈር ማድረግ ይጠበቅባቸዋክ፡፡

 

 1. ህብረተሰቡ የሚተላለፍ መልእክቶች፡-

 አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት)

 1. አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ምንድን ነው?

አተት በአይነምድር እና ትውከት ውስጥ በሚገኙ በአይን በማይታዩ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን ፤ በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን ፈሳሽ   አሟጦ በማስወጣት አቅምን የሚያዳክም በሽታ ነው፡፡  አፋጣኝ ሕክምና ካልተደረገ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡

 1. ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት አጋላጭ ሁኔታዎች፡-
 • የተበከለ ውሃ  
 • የተበከለ ምግብ
 • የግል እና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት
 • ሜዳ ላይ መፀዳዳት
 • የመፀዳጃ ቤቶችን በአግባቡ አለመጠቀም/አለመኖር
 1. የአተት በሽታ መተላለፊያ መንገዶች
 • በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የተበከለ የምንጭ፣ የጉድጓድ፣ የወንዝ፣ የዝናብ፣ የቧንቧ እና የሀይቅ ውሃን መጠቀም፣
 • በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የተበከለ የውሃ ማጠራቀሚያና መገልገያ እቃዎችን በአግባቡ ሳያፀዱ መጠቀም፣
 • በአግባቡ ባልታጠበ እጅ ምግብን ማዘጋጀት፣ ማቅረብና መመገብ፣
 • በበሽታው አምጪ ተህዋስያን የተበከለ ምግብ፣ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን መመገብ
 • ክዳን የሌላቸውና ለዝንቦች የተጋለጡ የምግብ ማስቀመጫና መመገቢያ እቃዎችን መጠቀም፣
 • የአተት ታማሚ ተቅማጥና ትውከትን በአግባቡ አለማስወገድ፣
 • አተት ታማሚ ጋር ንክኪ የነበራቸው ቁሳቁስ እና ተሸከርካሪዎችን በአግባቡ ሳፀዱ መልሶ መጠቀም፣
 • በአተት ምከንያት ህይወቱ ያለፈ ሰው አስከሬን ጋር ንክኪ ማድረግ፣
 1. የአተት በሽታ መከላከያ መንገዶች
 • ለመጠጥ  የሚውል ውሃን አፍልቶ በማቀዝቀዝ ወይንም በውሃ ማከሚያዎች አክሞ መጠቀም፣
 • ለቁሳቁስ ንፅህና መጠበቂያ የሚውል ውሃን አፍልቶ ወይንም በውሃ ማከሚያዎች አክሞ መጠቀም፣
 • የውሃ ማጠራቀሚያ እቃዎችን ሁልጊዜ በታከመ ወይም በፈላ ውሃ ማጠብ እና መክደን፤ 
 • ንጹህ የማብሰያ ዕቃዎች እና ሳህኖችን መጠቀም፣
 • ምግብን በደንብ አብስሎ በትኩስነቱ መመገብ ፣
 • ሳይበስሉ የሚበሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በታከመ ውሃ ማጠብና ወዲያውኑ መመገብ፣
 • የተረፉ ምግቦችዝንቦች እንዳይበከል  መክደን፣ በንፁህ ቦታ  ማስቀመጥ እና ከመመገብ በፊት ማሞቅ/ማንተክተክ
 • ለመብል የተዘጋጁ ምግቦችን ካልተዘጋጁ ምግቦች ለይቶ ማስቀመጥ፣   
 • በሚከተሉት ወሳኝ ጊዜያት እጅን በአግባቡ በሳሙና/አመድ እና በንፁህ ውሃ መታጠብ፡ 
  • ምግብ ከማዘጋጀት በፊት
  • ከመመገብ በፊት    
  • ለሕጻናት ጡት ከማጥባት ወይም ምግብ ከመመገብ በፊት
  • ሕፃናት ካፀዳዱ በኋላ
  • መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ    
  • በአተት ለታመመ ሰው እንክብካቤ ከተደረገ በኋላ
  • በአተት ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ ሰው አስክሬን ጋር ንክኪ ከተፈጠረ በኋላ
 • መጸዳጃ ቤቶችን መጠቀም፣ በንጽህና መያዝ እና ከተጠቀሙ በኋላ መክደን
 • የሕጻናትን ዓይነ ምድር መጸዳጃ ቤት ውስጥ መድፋት፣ ወይም ጠለቅ ያለ ጉድጓድ ቆፍሮ መቅበር
 • የታማሚውን ተቅማጥ እና ትውከት በአግባቡ መቀበል፣ መጸዳጃ ቤት ውስጥ መድፋትና ከጨረሱ በኋላ እጅን በሳሙና እና በውሀ በደንብ መታጠብ
 • ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ
 1. የበሽታው ምልክቶች
 • በድንገት የሚከሰት ብዛት ያለው አጣዳፊ ውሃ መሰል ተቅማጥ (የሩዝ ውሃ የሚመስል)
 • በተደጋጋሚ ማስመለስ
 • አተት ትኩሳት ወይንም የቁርጠት ህመም ላይኖረው ይችላል ፤ ይሁን እንጂ ቶሎ ህክምና ካላገኘን በሰውነታችን ያለው ፈሳሽ ተሟጦ ሰለሚያልቅ የአቅም ማነስ ፣ የቆዳ መሸብሽብ ፣ የአይን መሰረጎድ፣ የአፍ መድረቅ ብሎም ሞት ያስከትላል፡፡
 1. በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ወቅት ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች
 • ከምልክቶቹ አንዱ በታዬ ጊዜ ወደ ህክምና ተቋም እስክንደረስ ድረስ ቤት ውስጥ የሚገኘ ማንኛውንም ንጽህናው የተጠበቀ ፈሳሽ መውሰድ ያስፈልጋል፤
 • .አር.ኤስ በቤት ውስጥ ከሌለ 6 የሻይ ማንኪያ ስኳር እና ግማሽ የሻይ ማንኪያ ጨው በአንድ ሊትር ንጹህ ውሃ በመበጥበጥ ባስቀመጠ ቁጥር መጠጣት
 •  .አር.ኤስ በቤት ውስጥ ካለ አንድ ፓኬት ተፈልቶ በቀዘቀዘ አንድ ሊትር ውሃ በመበጥበጥ መጠጣት፤ .አር.ኤስን መጠቀም የሚቻለው በተበጠበጠ 24 ሰዓት ውስጥ ብቻ ነው።
 • ጡት የሚጠቡ ህፃናት በበሽታው ከተያዙ ጡት ማጥባቱን ከወትሮው በመጨመር መቀጠል፣

 

ለተጨማሪ መረጃና ምክር አገልግሎት በነፃ የስልክ መስመር፡

952 ወይም 8335 ይደውሉ

 • Twitter icon
 • YouTube icon
 • Facebook icon
 • Flickr icon