የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ከ58 ወረዳዎች ወባን ጨርሶ ለማስወገድ የሚያስችል መርሃ ግብር ይፋ አደረገ

 

 

 
የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየሁ

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየ መርኃ ግብሩን  በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ባልተስፋፋበት እንዲሁም የህክምና መድሃኒቶችና ግብአቶች ባልተሟሉበት ወቅት የወባ በሽታ ያደረሰው የህመምና የሞት መጠን የማይረሣ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል ብለዋል፡፡

 

እንደ ቢሮው ኃላፊ ገለፃ መንግስት፣ማህበረሰብ እና አጋር ድርጅቶች በተቀናጀ ሁኔታ በመስራታቸው የወባ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል ስኬታማ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉ ሲሆን በዚህም በክልሉ በ2005 ዓ.ም 1.2 ሚሊዮን ሰዎች የወባ ህሙማን ቁጥሩን በ2009 ዓ.ም ወደ 387,096 ማውረድ ተችሏል ብለዋል፡፡

 

እስካሁን የታየው አበረታች  ለውጥ በሽታው  የህብረተሰብ የጤና ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ልናደርሰው እንደምንችል ታላቅ አቅም እንዳለን አመላካች በመሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላትና የማህበረሰብ ክፍል ተቀናጅቶ የወባ በሽታን ጨርሶ የማስወገድ ተግባሩ ላይ ሊረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ በበኩላቸው እንደተናገሩት የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ህብረተሰቡ ስለሆነ የወባ በሽታን ጨርሶ በማስወገድ ተግባራት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ክልሉ አልፎም አገሪቱ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት በክልሉ መንግስት ስም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

 

በአገር አቀፍ ደረጃ ወባን ጨርሶ ማስወገድ የሚያስችለውን ፍኖተ ካርታ (road map) ያቀረቡት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወባን ጨርሶ የማስወገድ መርኃ ግብር አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደረጀ ድሉ እንደተናገሩት አሁን ላይ በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል የተገኘው አገራዊ 

ስኬት በሽታውን ጨርሶ ለማጥፋት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደምንገኝ ገልጸው በቀጣይ የህብረተሰቡ የአጎበር አጠቃቀሙን እንዲያሻሽል ግንዛቤውን ማጎልበት ፣ ተገቢውን የህክምና ግብአት ማሟላትና የህክምና አገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ማሻሻል  ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

 

አንደ አቶ ደረጀ ድሉ ገለፃ ወባን ጨርሶ የማስወገዱ መርሃ ግብር በአማራ ክልል በሦስት ዞኖች(በሰሜን ወሎ፣በደቡብ ወሎ፣በሰሜን ሸዋ እና በደሴ ከተማ አስተዳደር) እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ  በ239 ወረዳዎች እንደሚተገበርና ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 ከወባ ነፃ ለመሆን የሚያስችል ራዕይ  አንግባ እንደምትንቀሳቀስ ተናግረዋል፡፡ 


ዜና ማህደር ዜና ማህደር