በኢትዮጵያ በእናቶችና ህፃናት ጤንነት ላይ የሚመክር አለም አቀፍ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

ለእናቶችና ህፃናት ህይወት አስከፊ የሆኑ መሰናክሎችን ለመቅረፍNews ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በቅንጅትና በህብረት መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኘሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በዛሬው ዕለት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አራተኛውን 'አክቲንግ ኦን ዘ ኮል' በሚል ርዕስ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ትኩረቱን ያደረገውን ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት እንዳስታወቁት የእናቶችና ህፃናት ሞትን በመቀነሱ ረገድ ኢትዮጵያ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ኘሬዝዳንቱ አያይዘውም የእናቶች እና የህፃናትን ህይወት ለመታደግ ሁሉም ሀገራት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበው ባለፉት ጊዜያት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች የተነሣ በኢትዮጵያ የእናቶች ሞት 72 በመቶ እንዲሁም የጨቅላ ህፃናት ሞት ደግሞ እ.ኤ.አ ከ1990 እስከ 2015 ባሉት ጊዜያት በግማሽ ሊቀንስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ጤና ነክ ጉዳዮች  ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየና እየተሻሻለ መምጣቱ ሀገሪቷ እየተከተለች ያለችው የጤና ፖሊሲ ውጤታማነት እንደሆነ ገልፀው በዚህም ሀገሪ~  ሁሉንም አስቀድሞ መከላከል የሚቻሉ የእናቶችና የህፃናት ሞትን ሙሉ በሙሉ እ.ኤ.አ በ2035 ለማጥፋት እየሠራች እንደሆነ ኘሬዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡

የህንድ የጤና ጥበቃ እና የቤተሰብ ደህንነት ሚኒስቴር ሚስተር ሻርማን ጆላኒ በበኩላቸው የህንድ መንግስት የሀገሪቱን ህዝቦች ጤንነት ለመታደግ ይቻለው ዘንድ ልዩ ልዩ ስትራቴጅዎችን በመንደፍ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በህንድ ከአስር እናቶች መካከል ስምንቱ በጤና ተቋማት የሚወልዱ ሲሆን የማህበረሰቡን የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ይቻል ዘንድ የሚከናወኑ ሥራዎች ውጤት እያመጡ እንደሆነ ተሞክሮአቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኘሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ሁለገብ ተግባራት ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው የእናቶችና ህፃናት ጤንነትን ለመታደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በህንድ ጤና የጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና በአጋር ድርጅቶች ቅንጅት የተዘጋጀው ይህ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ከ15 ሀገራት የተውጣጡ 500 ተሣታፊዎችን በማሳተፍ ለሁለት ቀናት እንደሚከናወን ታውቋል፡፡


ዜና ማህደር ዜና ማህደር