የድብርት ህክምናን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ

Newsየዘንድሮ የአለም የጤና ቀን በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች በየካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ተከብሯል፡፡ በድብርት ላይ እንነጋገር በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከአለም ጤና ድርጅት፣ ከአርቲስቶች፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡

ድብርት በታዳጊዎች እና ወደ ጉርምስና በመግባት ላይ በሚገኙት ላይ መጠኑ የሚጨምር ቢሆንም በማንኛውም ሰው ላይ ሊደርስ የሚችል ነገር ግን መከላከል የምንችለው የአእምሮ ጤና ችግር ነው፡፡ በፆታ ደረጃ ሲታይ ሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጥቃት ከወንዶች በ50% ይበልጣል፡፡ የድብርት መንስኤዎች ብዙ ቢሆኑም የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ከዘር የሚተላለፍ፣ የውስጥ ህመሞች፣ ለራስ የሚሰጥ አሉታዊ ግምት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ከጥናቶች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በአለም በየቀኑ 3,000 የሚሆኑ ሰዎች በድብርት ምክንያት ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ ከ4 ሚሊዮን በላይ የድብርት በሽታ ተጠቂዎች ያሉባት አገራችን በተጠቂዎች ቁጥር ከአፍሪርካ አገራት ውስጥ ከናይጄሪያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ህክምና የሚያገኙት 10% የሚሆኑት ብቻ መሆኑን የቀረበው ፅሑፍ የሚያሳይ ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው አገልግሎቱን የሚሰጡ የተቋማት እና የባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ካሱ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ከሚገኙት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል የድብርት ህመም አንዱ ነው ብለዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ይሄንን ችግር በመረዳት ከአጋር ድርጅቶችና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በተሻለ ሁኔታ ለመስራት የ5 ዓመት የአእምሮ ጤና ስትራቴጂያዊ እቅድ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ጨምሮ ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአለም ጤና ድርጅት ጽ/ቤት ተጠሪ ዶ/ር አክ ፓክ ካሉ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት የአእምሮ ጤና ችግሮች ላይ ለመስራት ያሳየው ቁርጠኝነት የምያስመሰግን መሆኑን ገልፀው እየተደረገ ያለውን ጥረት የአለም ጤና ድርጅት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ በድብርት የሚመጡ ችግሮችን በተመለከተ ዶ/ር ካሉ በቤተሰባቸው ውስጥ ተከስተው የነበሩ ገጠመኞችንና ችግሮቹ የተፈቱበትን ተሞክሮ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡ የድብርት ተጠቂ የሆነውን ሰው መቅረብ፣ ማወያየትና ማገዝ ቁልፍ የመፍትሔ እርምጃዎች መሆናቸውን አስምረውበታል፡፡


ዜና ማህደር ዜና ማህደር