የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ ተደነቀ

የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ ተደነቀ

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ መርሀ ግብር ውጤታማ ይሆን ዘንድ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በመጠቀም ለህዝቦቿ እየሰጠች ያለችው የጤና ግልጋሎት በ71ኛው ዓለም አቀፍ የዓለም ጤና ድርጅት ስብሰባ ላይ ከፍተኛ አድናቆትን ማግኘቱ ተሰማ፡፡

ሠሞኑን በስዊዘርላንድ ጀኔቫ እየተከናወነ ባለው የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ እንደተገለፀው ዓለም አቀፉ ማህበረተሰብ ውጤታማ ከሆነው ከኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ሊማር የሚገባቸው በርካታ ተሞክሮዎች እንዳሉ ተገልጿል፡፡

ከመላው ዓለም ሠሞኑን ጄኔቫ የከተሙት የየሀገራቱ የጤና ሚኒስትሮች፣ዳይሬክተሮችና የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በጤና ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዓለም አቀፉን የጤና ሽፋን ውጤታማ ለማድረግ ይቻል ዘንድ አማራጭ የሆነው መንገድ መሠረታዊ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ መርሀግብሮችን ሁሉም ሀገራት ለህዝቦቻቸው መተግበር ሲችሉ እንደሆነ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ይኸው ዓለም አቀፍ ጉባዔ የኢትዮጵያን ልምድ በውጤታማነቱ በማንሣት ሀገራት ከኢትዮጵያ በጐ ተሞክሮ ትምህርት መቅሰም እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

ዶ/ር ከበደ ወርቁ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ በዚሁ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት የጤናው ሥርዓት ይበልጥ ውጤታማ ይሆን ዘንድ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ የጤና ተቋማት ግንባታዎችን ለማከናወን እና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ቁጥርን በመጨመር ተደራሽነታቸውን ለማስፋት በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አስታውቀዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የናምቢያው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር በርናርድ ሀውፋኪ በበኩላቸው ሀገራቸው የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በቅርበት በማየትና በመከታተል ፕሮግራሙን ወደ አገራቸው በመውሰድ ለሀገራቸው በሚስማማ መልኩ በመተግበራቸው ውጤታማ መሆናቸውን ለስብሰባው ተካፋዮች መስክረዋል፡፡ በዚህም የዜጎቻቸው የጤና ሁኔታ መሻሻሉን አብራርተዋል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በበኩላቸው የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ለዓለም አቀፉ የጤና ሽፋን ውጤታማነት መሠራቱ እንደሆነ ተናግረው የዓለም ጤና ድርጅት የማህበረሰብ ጤና ሠራተኞችም የጤናው ሥርዓት አንዱ አካል እንዲሆኑ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ 

 


ዜና ማህደር ዜና ማህደር