የሚኒስትር ግለ ታሪክ የሚኒስትር ግለ ታሪክ

የሚኒስትር ግለ ታሪክ
H.E Prof. Yifru Berhan Mitke

ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ በ1965 በሰሜን ሸዋ ተወለዱ፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህራታቸውን በእነዋሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተልም በእግራቸው ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ከ60 ኪ.ሜ በላይ መጓዝ እና ትልቁን የአባይ ገባር የጀማ ወንዝን ማቋረጥ ግድ ይላቸው ነበር፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ውጣውረድ ቢያልፉም በትምህርታቸው ውጤታማ ከመሆን አላገዳቸውም፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ በ1990 ዓ.ም የህክምና ትምህርታቸውን በከፍተኛ ማዕረግ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ዓለም ተቀላቀሉ፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ፣ የማህጸንና ስፔሻሊስት ሃኪም፣ በትምህርት ማዕረጋቸውም የማህጸንና ጽንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ በ1990 ዓ.ም በጌዴዮ ዞን የቡሌ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ሃላፊ፣ ከ1991-1992 ዓ.ም የዲላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፣ ከ1998-2007 ዓ.ም የሃዋሳ ዩንቨርሲቲ ሴኔት አባል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፣ ከ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ ባሳለፏቸው የስራ ጊዜያት ሙያዊ ስነምግባርን ተላብሰው ተገልጋዮችን በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ በአንድ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ በጌዲዮ ዞን የተከሰተውን የታይፎይድ በሽታን የአካባቢውን ማህበረሰብ፣ የክልልና የፌዴራል አመራር አካላትን በማስተባበር በሽታው እንዲቀለበስና የዜጎችን ህይወት ለማትረፍ ሌት ተቀን የተረባረቡና በህዝብ ቀልብና ልብ ውስጥ የገቡ ባለሙያ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ከ2004 ጀምሮ የግል ጥቅማቸውን ወደ ጎን በመተው በሃዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ከ10 ሰዓት እስከ 12፡30 ድረስ የነጻ ህክምና አገልግሎትን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለማህበረሰቡ የሰጡ ምስጉን ባለሙያ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ከ70 በላይ የምርምር ጽሁፎችን በግልና በቡድን በታወቁ ጆርናሎች ያሳተሙ ምሁር  ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ባዘጋጁት ፕሮፖዛል ከኔዘርላንድ መንግስት 12 ሚሊዮን ብር ልናገኝ ችለናል፤ በተጨማሪም ከዓለም ጤና ድርጅትና ከዩኒሴፍ 5.6 ሚሊዮን ብር ለልዩ ልዩ የኤች አይ ቪ ስራዎች የሚሆን ፕሮፖዛል ከ5 ባልደረቦቻቸው ጋር በመቅረጽ የደቡብ ክልል ህዝብን ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡

ፕሮፌሰር ይፍሩ ከላይ በተጠቀሱት የትምህርትና አመራር ዘርፎች በመሰማራት በጤናው ልማትና ምርምር ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ በቅርቡ በተመደቡበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ጤና ሳይንስ ሃላፊነት ጉልህ ውጤት ማምጣት የጀመሩ ተመራማሪ፣ መምህርና ሃኪም ሆነው ሰርተዋል፡፡