ጋዜጣዊ መግለጫ

በኮሮና ቫይረስ በሽታ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ


የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ በሽታ ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ እርምጃዎች አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይህም ለህብረተሰቡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት እንዲደርስ የተደረገ ቢሆንም ምክረ-ሃሳቦቹን የበለጠ ግልፅ ለማድረግና በህብረተሰቡ ዘንድ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቆዎችን ለማብራራት የዛሬውን የሚዲያ ገለፃ ማድረግ አስፈልጓል፡፡ 

የኮሮና ቫይረስ በሽታ በሃገራችን አሁንም የማህበረሰብ ጤና ስጋት ነው ፤ በውል ለማይታወቅ ጊዜም ስጋት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በሽታው በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ከ 900 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሁሉም የእድሜ ክልል፣ የጉዞም ታሪክ ሆነ ከታመመ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው የኮቪድ-19 ታማሚዎች በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተገኝተዋል። በሃገራችን የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታትና በሽታው በህብረተሰቡ ጤናና በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መንግስት በሽታው ወደ ሃገር መግባቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ ሲወስድ መቆየቱ ይታወሳል።
በተሰሩትም በርካታ ስራዎች በሽታው በተከሰተ በመጀመሪያዎቹ ወራት እና አሁን ላይ ያለው ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ በወቅቱ በሽታው አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ስለበሽታውና በሽታውን ለመከላከል ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲሁም በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለመርዳት ስሚወሰዱ እርምጃዎች የነበረው እውቀትና ዝግጁነት በአለማቀፍም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ውሱን ነበር፡፡ እንደሀገር የነበረን የምርመራና የህክምና መስጫ ተቋማት አቅም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ በሽታውን ለመከላከል የሚስፈልጉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ምርትና አቅርቦት እጅግ ዝቅተኛና የብዙ አገራት ፉክክር የሞላበት ነበር፡፡ በሽታው በሃገራችን ውስጥ ስርጭቱና ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት መተንበይ የሚቻለው ከሌሎች ሃገሮች ልምድ በመነሳት ላይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ በሽታው በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የሞትና የህመም ጉዳት ያደርሳል የሚል ትንበያ ነበር፡፡ 

በሽታውን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር አሁን ያለንበትን ደረጃ ስንመለከት ህብረተሰቡ ዘንድ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ አሁንም ቀጣይ ስራ የሚፈልግ ቢሆንም ተሻሽሏል፤ የማስክ አጠቃቀምና ሌሎች ጥንቃቄዎች የመውሰድ ባህልም ገና በቂ የሚባል ባይሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በሽታውን ለመከላከል የሚስፈልጉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አቅርቦት ተሻሽሏል፡፡ በየአከባቢው ህብረተሰቡን የሚያስተምሩና ድንገተኛ ምላሽ የሚሰጡ ቡድኖችን ማደራጀት ፤ የምርመራ አቅማችን የማሳደግ፤ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለመርዳት የተሻለ የህክምና አቅም መገንባት፤ በየደረጃው የዘርፈ-ብዙ ምላሽም ማጠናከር ተችሏል፡፡ 

በሌላው ጎን የኮቪድ-19 በሽታ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን ሊቆይ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አሳውቋል። በሃገር አቀፍ ደረጃ ቀደም ብለው የተወሰዱት ጠንካራ እርምጃዎች የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እጅግ ያገዙ ቢሆንም የህብረተሰቡ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ተጽዕኖቹ መልሰው የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት በከፋ መልኩ መጉዳታቸው የማይቀር ነው፡፡ በሽታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠፋ የማይችልና ረዘም ላለ ጊዜ የህብረተሰብ ጤና ስጋት ሆኖ ሊቆይ የሚችል እንደሆነ የአለም ጤና ድርጅትና ሌሎች አለማቀፍ ድርጅቶች ማሳወቃቸው ሊደርስ የሚችለውን ተፅኖ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

ስለዚህም ቀጣይ እርምጃዎችን አስመልክቶ የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ የጤና ሚኒስቴርና፤ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ19 ግብረ ሀይል በመረጃ ላይ የተመሰረተ ጥናት ሲያደረግና ፤ የኮሮና ቫይረስ ባለሙያዎች አማካሪ ካውንስሉን፣ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ያሉ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎችን ሲያማክር ቆይቷል፡፡ በጥናቶቹም በሁሉም የተደረሰው ድምዳሜ የኮሮና በሽታ የሚቆይ ከመሆኑ ጋርና ከላይ የገለጽኩት አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት፤ ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች የጎንዮሽ ተጽእኖ የከፋ እንዳይሆንና የመከላከል እርምጃዎቹን ጎን ለጎን በማስኬድ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መክፈት አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡ የተወሰዱ እርምጃዎች/ክልከላዎች አነሳስ የየአካባቢውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እና አተገባበራቸውም በሂደት ሆኖ፣ የማስክ አጠቃቀም፣ የአካላዊ ርቀት እንዲሁም የእጅ ንጽህና አጠባበቅ ሁኔታዎች የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው መስፈርት መሰረት ባሟላ መልኩ እንዲተገበሩ በማድረግ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ አሁን ተዘግተውና ተገድበው ያሉ አገልግሎቶችና እንቅስቃሴዎች ከከፍተኛ ጥንቃቄና በቂ ዝግጅት ጋር በሂደት መልሰው ሊጀመሩና ሊከፈቱ እንደሚችሉ አመላክቷል፡፡ ክልከላዎች እንደ አስፈላገነቱ ቢነሱም ቀጣዩን ጊዜ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረጉ እርምጃዎች ለማስተግበር የሚያስችሉ መመሪያዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ መመሪያዎች እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

የጤና ሚኒስቴርም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ምክረ ሃሳብ በእነዚህ ጥናቶች፣ የአለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች አለማቀፍ ድርጅቶች ባወጡዋቸው መመሪያዎችና ምክረ ሃሳቦች እንዲሁም በሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ላይ  በመመርኮዝ ነው፡፡ 

ከላይ የተጠቀሱት እንዳሉ ሆኖ  የኮሮና በሽታ አሁንም እየተሰራጨ ያለ አደገኛ የህብረተሰብ ጤና ስጋት እንደሆነ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በድጋሚ እየገለጽኩ፤ አሁን የምናደርጋቸው የክልከላ ማሻሻያዎች ከላይ የጠቀስኳቸውን ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ እንጂ በሽታው ስለቀነሰ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡  ስለሆነም አሁንም ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል፣ የመንግስተና የግል ተቋማት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው ማሳሰብ እወዳለው፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን በአንዳንድ የትራንፖርት አገልግሎቶች፣ በካፌ፣ ሬስቶራንት፣ ምግብ ቤቶችና መዝናኛ ቤቶች የምናናየው ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በአጽንኦት ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡  

በመጨረሻም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እስከ ዛሬዋ እለት ላበረከታችሁት እጅግ የላቀ አስተዋፅኦና መስዋእትነት እያመሰገንኩ ወደፊትም ከፊታችን የተጋረጠብን የኮቪድ-19 አገራዊ ፈተና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲያልፍ በእያንዳንዷ ደቂቃ የምናከናውነው ቅድመ ጥንቃቄ በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ መሆን እንዳለበት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ የእጅ ንፅህናን በመጠበቅ በተለይም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በአግባቡ በመጠቀም እንፈጽም!

አመሰግናለሁ! 
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚንስትር፤ መስከረም 11/2013 ዓ.ም.
 

Amharic