ጋዜጣዊ መግለጫ

የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን እንዳይገባ ዝግጅቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን በተመለከተ የተዘጋጀ መግለጫ  


እስከጥር 18, 2012 ዓ.ም. ድረስ ያለው የኖቨል ኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታ
በዓለም የጤና ድርጅት ዕለታዊ ሪፖርት መሰረት በሽታው በወረርሽኝ መልክ ሪፖርት መደረግ የጀመረው ከታህሳስ 24፡ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን እስከ ዛሬ ጥር 18፡ 2012 ድረስ በጠቅላላው 2700 ሰዎች በበሽታው የታመሙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የሰማኒያ (80) ሰዎች ሕይዎት ማለፉ ታውቋል፡፡  በሽታው ወደ ሀገራቸው መግባቱን ሪፖርት ያደረጉ ሀገራት ቁጥር 11 ደረሶዋል።

ቫይረሱ ወደ ሀገራችን እንዳይገባ ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት፡ 

 • በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከ ቻይና እና አጎራባች አገሮች ለሚመጡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ (thermal screening)  እና ፎርም የማስሞላት ስራ ተጀምሯል፡፡ የልየታ ስራውን ለማጠናከር በቂ የሰው ኃይል ተመድቧል፡፡ 
 • እስከ ዛሬ (18/05/2012) ድረስ ጠቅላላ ለሃያ ሺ ስምንት መቶ ሁለት (20,802) መንገደኞች ልየታ የተደረገላቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አምስት መቶ ሃምሳ ሁለቱ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ካለባቸው ሀገራት የመጡና ለዚህ ስራየ ተዘጋጀውን ቅፅ ሞልተው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ እና ክትትል የሚደረግባቸው መንገደኞች ናቸው፡፡
 • እስካሁንም በአጠቃላይ ከ ቻይና የመጡ 4 የተጠረጠሩ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማእከል ተለይተዉ ክትትል እየተደረገላቸዉ ነው። ከተለዩት ተጠርጣሪዎች ሁለቱ የሳል እና የሙቀት ምልክት ያሳዩ ቢሆኑም በአሁኑ ሰአት ግን አልፎ አልፎ ሳል ከማሳየታቸዉ ዉጭ ሌላ የበሽታ ምልክት የላቸውም። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ምንም አይነት የህመም ምልክት ባያሳዩም ከ ቻይና ወረርሽኙ ካለበት ቦታ የመጡ መሆናቸዉ እና ከ ምልክቱን ካሳየዉ ተጠርጣሪ ጋር ቅርብ ግንኙነትያላቸዉ መሆኑ ተለይተዉ ክትትል እየተደረገላቸዉ ነው፡፡
 • ከአራቱ ተጠርጣሪ ህመምተኞች የላብራቶሪ ናሙና ተወስዶ ለምርመራ በዛሬው ዕለት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳል። ከተወሰደው ናሙና በአገራችን በተደገላቸው ምርመራ ከ 5 አይነት ኮሮና ቫይረሶች ነጻ መሆናቸውን ማወቅ ተችሎዋል።
 • በተለይም ከቻይና ለመጡ 280 መንገደኞች በየዕለተቱ ባረፉበት ቦታ ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡ ዪሄም ክትትል ለ አስራ አራት ቀናት የሚቆይ ነው።
 • በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ክፍል ና የሰዉሃይልን ጨምሮ አስፈላጊዉ ግብአት ተዘጋጅቶዋል።
 • በበሽታው ለተጠረጠሩ መንገደኞች የጊዚያዊ ማቆያ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ ተዘጋጅቷል፤ 
 • የከፋ ሁኔታ ላለታየባቸው 30 ለሚሆኑ በበሽታዉ የሚጠረጠሩ ታካሚዎችን የሚይዝ የለይቶ ማከሚያ የህክምና መእከል በቦሌ ጨፋ ተዘጋጅቶ  አስፈላጊዉ የህክምና እና ልዩ ልዩ ግብአቶች እየተሟሉ ይገኛሉ። በዚህ ማእከል በሽታዉ የተረጋገጠባቸዉ፣  የተጠረጠሩ እና ተለይቶ ክትትል ለሚደረግላቸዉ ክፍሎች ተለይተው ተዘጋጅቶዋል
 • በጽኑ ለታመሙና ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸዉ ታካሚዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል ተዘጋጅቶዋል
 • በጤና ሚኒሰቴር የሚመራ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ የወረርሽ ቅድመ ዝግጅት ብሄራዊ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የመጀመሪያ ውይይቱን ያደረገ ሲሆን ውይይቱ ሌሎችን በማካተት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡በዚህ ግብረ ሃይል የተካተቱት ፤ አዲስ አበባ መስተዳድር፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ቀይ መስቀል፣ ባህል እና ቱሪዝም ፣ ኢሚግሬሽን እና ሌሎች አግ ባብነት ያለቸው ይገኙበታል ።
 • በኢትዮያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚመራ የቴክኒካል ቡድን ተቋቁሞ ስራዉን ጀምራል፡
 • በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ለኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅት የአደጋ ማስተባበሪያ ማእከል (Emergency Operation Center ) ወደ ተግባር በማስገባት ጭምጭምታዎችን የማረጋገጥ እና ለተጠርጣሪዎች ጥልቅ ምርመራ እየተሰራ ነው
 • በመደበኛነት የዓለማችንን ወቅታዊ ሁኔታ ክትትል በማድረግ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ወቅታዊ መረጃ እና ምክረ ሃሳብ እየተሰጠ ነው፡፡  
 • የክልል እና የከተማ ጤና ቢሮዎችን አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ በኢሜልና በደብዳቤ የአለም የጤና ድርጅት ምክረ ሐሳቦችን መሰረት ያደረገ የማንቂያ ምልዕክት አስተላለፈናል፡፤
 • የዝግጁነትና ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ የትግበራ እቅድ ተዘጋጅቷል
 • ለባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠና መስጠት ተጀምሮዋል፡፡
 • የሕብረተሰቡን ስለ ቫይረሱ ወረርሽኝ ለማንቃት ና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ወቅታዊ መረጃዎችን ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ክትትልም ይደረጋል፡፡ 
 • የጋዜጣዊ መግለጫ የመስጠት እና ሕብረተሰቡን፣መንገደኞችን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን  የማንቃት፣አስፈላጊ የኮሚኒኬሽን ማቴሪያሎችን የማዘጋጀት እና የማሰራጨት ተግባራት ከመከናወናቸውም በላይ ከአፍሪካ ሲዲሲ እና የዓለም የጤና ድርጅት ጋር በምክር እና ሪኤጀንትን በመተለከተ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0112765340  ወይም በኢሜል አድራሻችን 
phemdatacenter@gmail.com ወይም ephieoc@gmail.com በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡


ጤና ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ዒንስቲትዩት
ጥር 19, 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ

 

Amharic