ጋዜጣዊ መግለጫ

        በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ
                                                   ግንቦት 20/2012 ዓ.ም


ዓለም አቀፍ የወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ቀን "በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጌዜም ቢሆን የወር አበባ አይቆምም  ጌዜው አሁን ነው!" በሚል መሪ ቃል  በሀገራችን  ይከበራል፡፡  
የዘንድሮው በዓል አከባበር ዋና ዓላማው ለሴቶችና ለልጅአገረዶች በተለይም ከየአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ፣በመጠለያ ካምኘ ላሉ እንዲሁም በለይቶ ማቆያና ለይቶ ማከሚያ ማዕከላት ለሚገኙት ሴቶችና ልጃገረዶች በወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ዙሪያ የሚደረገው ድጋፍ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅትም ቀጣይነት ያለው መሆኑን አጉልቶ ለማሳየት ነው ፡፡ 


እንደ ኮቪድ 19 ያሉ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች የወር አበባን ወቅቱን ጠብቆ ከመታየት አያቆሙም፤ ስለሆነም የሴቶችን ፣የልጃገረዶችንና ከወረርሽኙ ጋር እየታገሉ ያሉትን ግንባር ቀደም የሴት ጤና ባለሙያዎችን መሠረታዊ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ፍላጎቶችን ለመደገፍ የሚሰሩ ስራዎችንም ሊያቆም አይገባም፡፡ 


ከየአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ፣በመጠለያ ካምኘና በለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንዲሁም በየጤና ተቋማት ላሉ ሴቶችና ልጃገረዶች በሙሉ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ማዳረስ  እንዲሁም በገጠር አካባቢ ለሚገኙ ልጃገረዶችም በአካባቢያቸውና በቤታቸው ከሚገኙ ቁሳቁስ  ንጽህናው የተጠበቀ የወር አበባ መጠበቂያ እንዴት እንደሚሠራ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡


ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የጤና ሚኒስቴር መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በወር አበባ ንጽህና አጠባበቅና ጤና ኘሮግራም ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ኘሮግራም ከወር አባባ ጋር ተያይዞ ያለውን መሳቀቅና መገለል ለመቅረፍ በት/ቤቶችና በማህበረሰብ ውስጥ በወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራዎችን ያካትታል በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች የውሃና የመጸዳጃ ቤት አቅርቦትንና የማሟላት ፣ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማዳረስንና  በወር አበባ ጊዜያቸው ከት/ቤት የሚቀሩትን ልጀገረድ ተማሪዎችን ለመቀነስ ለወር አበባ ንጽህና መጠበቂያና ማረፊያ የሚያገለግል በቂ ክፍል ማዘጋጀትን ያጠቃልላል፡፡


ከወር አበባ ጋር ተያይዞ በተለይም በገጠሩ ክፍል ያለውን ከባህል ጋር የተቆራኘ መገለልን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የ2012ዓ.ም የ‘’CNN’’ ጀግና የሆነቸውን የፍሬወይኒ መብራሀቱን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተከትሎ የኢትዬጱያ ፌደራላዊ ርዕሰ ብሄር ክብርት ኘሬዜዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመሩት ግንባር ቀደም ብሄራዊ የወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ግብረኃይል ተቋቁሟል፡፡


በ2009 ዓ.ም ጤና ሚኒስቴርና ዩኒሴፍ በጋራ ባወጡት ሪፖርት መሠረት በኢትዬጵያ ከ10 ሴት ተማሪዎች ውስጥ ከአንድ በላይ ተማሪዎች በወር አበባ ምክንያት  ከትምህርት ቤት  ይቀራሉ ፡፡ በዚህ ሪፖርት እንደተመለከተው ከመቶ ሃያ ሁለት እናቶች ብቻ ከልጆቻቸው ጋር የመጀመሪያ የወር አበባ ከማየታቸው በፊት እንደሚወያዬ ሲያሳይ በተጨማሪ ከሦስት ሴት  ተማሪዎች አንዷ የተጠቀመችበትን የወር አበባ ንጽህና  መጠቀሚያ  ወደ ቤት ተመልሳ የምትቀይር ሲሆን  ይህም ሊሆን የቻለው ከግማሽ በላይ የሆኑት የት/ቤት መፀዳጃ ቤቶች የውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ነው፡፡


ከ2009 ዓ.ም የዳሰሳ ጥናት ወዲህ የወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ስራን ወደፊት ማምጣት ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የወር አበባ መጠበቂያዎች ደረጃ አገር አቀፍ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡

በተጨማሪም አዲስ የተከለሰው የት/ቤትና ጤና ተቋማት የውሃ የሣኒቴሽንና ሃይጅን የዲዛይን ግንባታ መመሪያ የወር አበባ ንጽህናንና አካል ጉዳተኞችን ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል፡፡


በመጨረሻም በወር አበባ ላይ ያለውን መገለል እንዲቆምና በዚህ ዓለም አቀፍ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ለተጋላጭ ሴቶችና ልጀገረዶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በማቅረብ   የበለጠ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ 


                                   "በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጊዜም  ቢሆን የወር አበባ አይቆምም"
 

Amharic