የጤናውን ሴክተር የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት እንዲረዳ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ የጤናዉ ዘርፍ አመራሮች የተሰጠዉ ስልጠና ብቃት ያላቸዉ አመራሮች ግንባር ቀደሙን ሚና እንዲወጡ እንደሚረዳ ተገለጸ፡፡
በሁለተኛዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመተግበር የታቀዱትን የጤናዉ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች በሚገባ ተገንዝቦ በእዉቀት ላይ የተመሰረተ አመራር ለመስጠት እንዲያስችል አምስት ሺ የጤናዉ ዘርፍ አመራሮች በአዲስ አበባ ፡ በባህርዳር፡ በአዳማ ፡በመቀሌና በሐዋሳ ከተሞች ለ20ቀናት የተሰጠዉን የመጀመሪያ ዙር ስልጠና አጠናቀዋል፡፡
የጤናው ዘርፍ አመራሮች የትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንዲሳካ የትኩረት አቅጣጫዎችን ተገንዝበዉ ለህብረተሰቡ ፍትሃዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ እንዲችሉ ስልጠናዉ ወሳኝ መሆኑን በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚ/ር የፖሊሲ ኘላን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኖህ ኤልያስ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ኖህ ገለፃ ለጤናው ዘርፍ እቅድ መሳካት አቅም ሊሆን የሚችለው የአመራሮችና የባለሙያዎች ስልጠና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ወደ ተግባር ምዕራፍ ሲገባም የተቀመጡትን አቅጣጫዎች በደንብ በመረዳት ከየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣምረዉ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዉ ፡ በተዋረድ የሚሠራውን ሥራ ለማገዝ የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክትትልና ድጋፍ ሥራዉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም በበኩላቸው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስልጠና በሐዋሳ ከተማ መሰጠቱን አስታዉሰዉ ፡ በክልላቸው የተከናወነዉን ስልጠና በማስተባበር ረገድ የበኩላቸዉን መወጣታቸዉን ገልጸዋል፡፡ ሰልጣኞቹ በተለይም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ህብረተሰቡ ፍትሐዊና ጥረቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በየስልጠና ቦታዎቹ በመገኘት ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተሳታፊዎች ከስልጠናው የጠለቀ እውቀት እንዳገኙና በተለይም በየጤና ተቋማቱ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑን መረዳታቸውን ገልዋል፡፡ በጤናው ዘርፍ የተቀመጡትን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች በብቃት ለመተርጎም ከአሁን ወዲያየተለያዩ ምክንያቶችን የምንደርደርበት እድል የለም ብለዋል፡፡
S'estàn mostrant 1 resultats.