የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ በመገኘት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎች የሚያገኙትን የጤና አገልግሎት በተመለከተ ምልከታ አካሄዱ 

  • Time to read less than 1 minute
Dr Dereje

በጥፋት ሀይሎች ለተጎዱ የጤና ተቋማትና በችግሩ የተፈናቀሉ ዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ  የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጻል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እና የሚኒስቴሩ የእናቶች እና ህጻናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ዶ/ር መሰረት ዘላለም ከኮንቦልቻ ከተማ ከንቲባ እና ከጤና መምሪያ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በመጠለያ የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝተዋል።


በጉብኝቱ ወቅትም ከዩኤንኤፍፒኤ (UNFPA) በድጋፍ የተገኙ 590ሺ ዶላር ግምት ያላቸው የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን፣ የስነ ተዋልዶ ኪቶችን፣ የኮቪድ መከላከያ ግብዓቶች የተረከቡ ሲሆን በርክክቡ ወቅትም ዶ/ር ደረጀ  ዱጉማ እንደተናገሩት  የጥፋት ሀይሎች በጤና ተቋማት ያደረሱትን ውድመት እና ዝርፍያ እንደዚሁም የበርካታ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን በዚህም ለተለያዩ የጤና ጉዳቶች መጋለጠቸውን ጠቅስው በዩኤንኤፍፒኤ (UNFPA) በኩል የተደረገው ድጋፍ በአስፈላጊ  ወቅት እና አካባቢ መደረጉንም ገልጸዋል። 


እንደ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ገለጻ የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር አካላትንጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ዩኤንኤፍፒኤ (UNFPA) ላደረገው ድጋፍን በጤና ሚኒስቴር ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


የሚኒስቴሩ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው የጥፋት ሀይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ ባደረሱት ጥፋት በርካታ ዜጎች ለጤና ጉዳት እየተጋለጡ እንዳለ አንስተው በተለይ እናቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ለተለያዩ ጤና ጉዳቶች እየተዳረጉ ነው ብለዋል።


በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እርጉዝ እናቶች እና ህጻናት ለምግብ እጥረት ችግር  እንዳይጋለጡ በጦርነት ወቅት ሊደረስ ከሚችል የተወሳሰበ የስነ ተዋልዶ ጤና ጉዳትም ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ  ተናግረው የጤና ሚኒስቴር  አጋር አካላትን በማሳተፍ በትኩረት እየሰራ  እንደሆነ ዶ/ር መሰረት አስረድተዋል።


በርክክቡ ወቅት የዩኤንኤፍኤ ካንትሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ  ዳኒያ ጋይለ  እንደተናገሩት ድርጅታቸው በጦርነት ወቅት ለልዩ ልዩ ጉዳቶች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን፣ ህጻናትን ፣ እርጉዝ እናቶችና ወጣቶችን ከከፋ የጤና ጉዳት ለመጠበቅ የተለያዩ  ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ተናገረው የተደረገው ድጋፍም  የዚሁ የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባር አካል መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።


የኮንቦልቻ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው በአካባቢው በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው  በጊዜያዊ  መጠልያ እንደሚገኙ ተናግረው ጤና ሚንስቴር አጋር አካላትን በማስተባበር እያደረግ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


በኮንቦልቻ ከተማ የሚገኘው ሆስፒታልም በግጭቱ ለተጎዱ ወገኖች እየሰጠ ያለው የህክምና አገልግሎም የተጎበኘ ሲሆን በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎችም የሚያገኙትን የጤና አገልግሎት በተመለከተ ምልከታ ተካሂዷዋል።